አንድ ሌሊት ‹‹በታህሪር››

ቀኑ ሐሙስ ነበር ፤ ከስራ ተመልሼ ቀን ከወዲያ ወዲህ እንጀራ ፍለጋ በመሯሯጥ የተዳከመዉን አካሌን በእንቅልፍ ፀጋ ላክም አልጋ ላይ ጋደም አደረግኩት፡፡ መቼም የደከመዉ ሰዉ እንዴት እንደሚተኛ ታዉቃላችሁ ፤ ዧ…ብሎ ነዉ የሚተኛዉ፡፡ በእንዲህ አይነት እንቅልፍ ዉስጥ ደግሞ ከጥልቅ የአዕምሮ እፎይታ በስተቀር ህልም ወይም ቅዠት የሚባል ነገር የለም፡፡ ነገር ግን ለምን እንደሆነ አላዉቅም ይህ በኔ ላይ አልተከሰተም ፤ ይልቁንም አካሌ ገና ጋደም ከማለቱ ትልቁ የአዕምሮየ ስክሪን ሙሉ በሙሉ ተዘረጋና እራሴን በመስቀል አደባባይ በትልቅ ህዝባዊ ማዕበል ዉስጥ ድንገት አገኘሁት፡፡

ቱኒዝያ ላይ ፈንድቶ የአረቡን አለም ያጥለቀለቀዉና የሚነካን የሚነቀንቀን የለም በሚል አጉል ስሜት ተወጥረዉ ስልጣናቸዉን ዘላለማዊ ስለማድረግ ያልሙ የነበሩትን አንጋፋ አምባገነኖች ያንቀጠቀጠዉና ከዙፋናቸዉ አሽቀንጥሮ የጣለዉ በእንቢታቸዉ የፀኑትን ደግሞ ወደ መቃብር የሸኘዉ ህዝባዊ መአበል በእኛም በአገራችን ፈንድቷል፡፡ ‹‹እሳት አመድ ወለደ›› ተብሎ የተተረተበትና የተቀለደበት ወጣት መዲናችን አዲስ አበባን ቀዉጢ አድርጓታል ፤ ሕዝቡ ከከተማዋ አራቱም አቅጣጫወች እንደ ጉንዳን ወደ እኛዉ ‹‹ታህሪር›› /መስቀል አደባባይ/ ይተማል…ይተማል….ይተማል፡፡
ከህዝብ ብዛት አንፃር አዲስ አበባ በሚስጥር ደብቃ ያኖረችዉ ህዝብ አለ እንዴ!? ያስብላል፡፡ አደባባዩ አልበቃ ብሎ ህዝቡ ከስታዲየም እስከ ሜክሲኮ ፣ በደብረ ዘይት መንገድ እስከ ግሎባል ሆቴል እንዲሁም በቦሌ መንገድ እስከ ኦሎምፒያ ድረስ ተገጥግጦ በህብረት “የመለስ አንባገነናዊ አገዛዝ ይብቃ!” እያለ ይጮሃል፡፡ የጀግና አባቶቹ ወኔ ድንገት የተቀሰቀሰበት የሚመስል እልፍ አእላፍ ወጣት አይኑ በቁጣ ቀልቶ ከወዲያ ወዲህ እየተንጎራደደ ይፎክራል፡፡ አንዳንዶችም ቀንደኛ የሀገሪቱ መሪወችን ምስል እያቃጠሉ “…ሞት ለናንተ” እያሉ ይረጋግጡታል ፤ አመዱ እንደ አቧራ እየቦነነ በላዩ ላይ በስሜት ይዘላሉ፡፡

ከአደባባዩ አንድ ጥግ በእንጨት ማማ ላይ በቁጥር እስከ 20 የሚደርሱ ሰወች በረድፍ ቆመዉ ስሜት ቀስቃሽ መፈክር ያሰማሉ ፤ ምናልባት የተቃዉሞ አራማጆች ሳይሆኑ አይቀሩም፡፡ ከነሱ መካከል አንድ ጎልማሳ ሰዉ “የመለስ አንባገነናዊ አገዛዝ ይብቃ ፤ ሞት ለመለስና ጀሌዎቹ ፤ አንድነት ፣ ዲሞክራሲ ፣ ፍትህ እና እድገት ለኢትዮጵያ” እያለ በአማርኛና በኦሮሞኛ ቋንቋ መፈክር ያሰማል፡፡ ከሱ ግራና ቀኝ የተደረደሩ አጋሮቹም እያከታተሉ በሱማሌኛ ፤ በአፋርኛ ፤ በትግረኛ ፣ በጉምዝኛ… መፈክሩን ያሰማሉ፡፡ ከታች እንደ አሸዋ የተበተነዉ ህዝብም እንደ መብረቅ በሚያስገመግምና በሚያስፈራ ድምፅ መፈክሮችን ያስተጋባሉ፡፡

በአጠቃላይ የህዝብ ማዕበል ፣ የሚነድ ኢትዮጵያዊ ስሜት ፣ ጠንካራ ሕብረ ብሔራዊ አንድነት በአገዛዙ ላይ ፋፁም ተነስቷል፡፡ እኔም ያንን ኢትዮጵያዊ ስሜትና አንድነት ስመለከት ባለፉት ጊዚያት የስልጣን ጊዜን ለማራዘም ብቻ ተብሎ ይህንን ትልቅ ሀገራዊ ሀብት ለማደብዘዝ በአገዛዙ ሲፈፀም የነበረዉ እኩይ ተግባር ትዝ አለኝና በሳቅ እንከተከት ጀመር፡፡ ሳቄንም ሳላባራ “ለካ ኢትዮጵያዉያን በቁርጥ ቀን ፋፁም አንድ እና አንድ ናቸዉ” ስል ካጠገቤ ለቆመዉ ጓደኛየ ድምፄን ጎላ አድርጌ ተናገርኩ፡፡

ያንን በመሰለ ኢትዮጵያዊ ህብረ ብሔራዊ አንድነት እየተገረምኩና እየሳቅኩ ሳለ “ይገርምሀል እኮ ፤ ተቃዉሞዉ ዛሬ 6ኛ ቀኑ ነዉ” አለ ጓደኛየ በፊቱ ላይ ኩራት እየተነበበበት፡፡ ቀጠለናም “በመጀመሪያዉ ቀን መንግስት መዉሰድ የጀመረዉ እርምጃ ዘግናኝ ነበር፡፡ ሆኖም የአለም ማህበረሰብ ጭካኔዉን ሲያወግዝ የአሜሪካ መንግስት በአገዛዙ እየተወሰደ ያለዉ እርምጃ ባፋጣኝ ቁሞ የህዝቡ ጥያቄ በሰላማዊ መንገድ እንዲመለስ ተፅዕኖ በማድረጉ መንግስት ቀስ በቀስ እርምጃዉን ለመቀነስ ተገዷል፡፡ ህዝቡም ቢሆን እያደረ ቁጣዉ እየበረታ ሲሆን ፤ ከትናንት በስቲያ ጀምሮ ህዝባዊ አመፁ ወደሌላ አካባቢወች ተዛምቷል ፤ በየክልል ከተሞች ህዝቡ ቁጣዉ ገንፍሎ አደባባይ ወጦ ድምፁን እያሰማ ነዉ” አለ፡፡

በዚህ መሀል አይኔ አንድ ልቤን በደስታ ጮቤ ካስረገጣት ነገር ላይ አረፈ ፤ ይህም በወገናቸዉ ላይ ይፈፀም የነበረዉን በደል በግልፅ በመቃወማቸዉና ለፍትህና ዲሞክራሲ በመከራከራቸዉ በግፍ ወደ እስር ቤት የተወረወሩት ጀግና የህዝብ ልጆች ከቆምኩበት ቦታ በስተቀኝ በኩል ከህዝቡ ጋር መፈክር ያሰማሉ፡፡ ከነሱ መካከል ተወዳጁና በሙያዉ አንቱ የተሰኘዉ ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ አንዱ ሲሆን ፤ በፊቱ ላይ ደስታ እና እርካታ ይነበብበታል ፤ ፊቱን ከግራ ወደ ቀኝ እያዟዟረ ህዝቡን ይመለከታል፡፡ ጓደኛየ ትኩረቴ ከእስክንድር ላይ መሆኑን ሲረዳ ድምፁ እንዲሰማ ጮኾ “ከህዝብ በላይ ምንም ነገር የለም ፤ ህዝብ ቆርጦ ከተነሳ ሁሉም ይሆናል ፤ መንግስት አነዚህን የህዝቡ ልጆች እዲፈታ ስንት ሲለመን እንቢ ሲል ከርሞ በመጨረሻ የህዝቡ ቁጣ ገንፍሎ አደባባይ ‹‹ሆ›› ብሎ ሲወጣ ሳይወድ በግዱ ፈታቸዉ” አለ ፈገግ እያለ፡፡

ከአፍታ ቆይታ በኃላ አንዳች ተአምር ነገር እንደታየ ሁሉ ህዝቡ በታላቅ ድምፅ ደስታዉን ማስተጋባት ጀመረ ፤ ርችት በየቦታዉ መንጣጣት ጀመረ ፤ ከማማዉ እየተነሳ ወደ ሰማይ በመጎን በህብረ ቀለማት ቅርንጭፍጫፍ እየሰራ ወደታች በሚወርድ የርችት ብርሀን ሰማዩ ደመቀ ፤ አዲስ አበባ ፍፁም አይታዉ በማታዉቀዉ ሁኔታ ቀዉጢ ሆነች፡፡ በነገሩ እኔና ጓደኛየ ግራ ተጋብተን ከተያየን በኋላ ከአጠገባችን የኢትዮጵያን የጥንት ባንዲራ እያዉለበለበ በደስታ ወደ ሰማይ የሚዘልን አንድ ሎጋ ሰዉ “ምንድን ነዉ የተከሰተዉ ?” ስንል ጠየቅነዉ፡፡ ሰዉየዉም ደስታዉን ለመግለፅ እየተቸገረ በሚያምር የሱማሌኛ ቃና ባለዉ አንደበቱ “ጠቅላይ ሚኒስትራችን አገር ጥለዉ ‹‹እግር አዉጭኝ›› ወደ አሜሪካ ኮበለሉ ፤ ጀሌዎቻቸዉም የሳቸዉን ፈለግ እየተከተሉ ነዉ ፤ ከሀገር የተዉጣጣዉ ቡድንም ሀገሪቱን በግዜአዊነት ሊመራ ነዉ ፤ የአሜሪካ መንግስትም ጠቅላይ ሚኒስትሩንና ሌሎችንም ለፍርድ አሳልፈን እንሰጣለን ሲሉ ቃል ገብተዋል” አለና እንደገና ወደ ሰማይ እየጮኽ መዝለሉን ጀመረ፡፡ እኔም ከሱማሌዉ ወንድሜ ጋር አብሬ በደስታ እየዘለልኩ መጮህ ጀመርኩኝ፡፡

እንግዲህ በዚህ ቀዉጢ መሀል እያለሁ ነበር የሆነ ነገር ጎኔን ‹‹ጎሰም!›› ሲያደርገኝ ከእንቅልፌ ብንን ያልኩት፡፡ የመታኝ ከአጠገቤ በእንቅልፍ ልቧ የምትንከባለለዉ ሚስቴ እጅ ነበር ፤ በስሜት እራሴን በሁለት እጄ ጨብጨ ለአጭር ጊዜም ቢሆን በደስታ ተፍነከነኩኝ፡፡ ቆይቸ ግን ከእንቅልፌ በመንቃቴ በጣም ተቆጨሁ ፤ በየዋህነት ደግሜ ብተኛም ያንን ሕልም ለሁለተኛ ጊዜ ማየት አልቻልኩም፡፡ ሊነጋጋ ሲል ከዚያ አስደሳች ህልም በመንቃቴ እንዲሁም ደግሜ ማየት ባለመቻሌ ከልብ ስላዘንኩ ፍፁም እንቅልፍ ከአይኔ ጠፋ ፤ ስለሆነም ከአልጋየ ተነስቼ ካልወለቅኩ እያለ የሚያሰቸግረዉን አሮጌ ፒጃማየን በአንድ እጄ ጨምድጄ ይዤ ወደ መስኮቱ አቀናሁ ፤ ሁሌም የማብሰለስለዉ ሀሳብ ሲኖረኝ እንደማደርገዉ መስኮቱን ሙሉ በሙሉ ከፍቸ የዉጩን ቀዝቃዛ አየር ወደ ዉስጥ እየተነፈስኩ ወደ ሰማይ አንጋጥጨ መመልከት ጀመርኩ፡፡ ከአፍታ ቆይታ በኋላ በምስኪን ኢትዮጵያዊያን ላይ እየደረሰ ያለዉ ግፍ በአዕምሮየ አንድ ባንድ መምጣት ጀመረ ፤ ፈገግ አልኩኝ ፤ ከዚያም “አወ! የታህሪሩ ህልሜ ባይደገምም እዉን ግን ይሆናል” ስል ለራሴ አንሾካሾኩ፡፡

By Betre Yacob

Advertisements

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s