መስቀል የያዙ አጭበርባሪዎች ፤ የዛሬዋ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ድክመት መገለጫ

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ከሁለት ሽህ ዓመት በላይ ታሪክ ያላት ጥንታዊት ቤተክርስቲያን ስትሆን በኢትዮጵያ ታሪክ ዉስጥም ትልቅ ቦታ ይዛ የምትገኝ የታሪክ ደሴት ናት፡፡ ቤተክርስቲያኗ ጥንካሬዋን ጠብቃ የታሪክ ክብርና ሞገስ ሆና እዚህ እንድትደርስ ደግሞ ካህናትና መንፈሳዊ አባቶች የአንበሳዉን ሚና የተጫዉቱ ሲሆን ፤ የቤተክርስቲያንዋ ዋና ምሰሶዎች በመሆን አስተምሮተዋን  ሳይሸራርፉና ሳያዛንፉ በታማኝነት እየተቀባበሉ ዘመናትን አሻግረዉ ዛሬ ላይ አድርሰዋታል፡፡ የዛሬወቹ ባላደራወችም ይህንኑ የማስቀጠል ትልቅ መንፈሳዊ አደራ ከምን ግዜዉም በላይ ተሸክመዉ ጉዞዉን ጀምሯል፡፡ ሆኖም ከቅርብ ግዜ ወዲህ በሚያሳዝን ሁኔታ ይችን ዘመናትን ተሻግራ ዛሬ ላይ መቆም የቻለች ቤተክርስቲያን ሊያደናቅፍና ስሟን ጥላሸት ሊቀባ የሚችል ፀያፍ ስራ አንዳንድ መንፈስ ቅዱስ ተገለጠልን በሚሉ በራሷ ሰዎች /ባላደራወች/ ሲፈፀም መታየት ጀምሯል፡፡

እኒህ ሰዎች የተከበረዉን ቀሚስ ለብሰዉ ፣ ቆብ ደፍተዉ ፣ መቋሚያና መስቀል በቀኝና በግራ እጃቸዉ ጨብጠዉ ፣ ጢማቸዉን አንዠርግገዉ አባ ፣ መምህሬ ፣ ቄስ ፣ መነኩሴ ፣ ባህታዊ… እየተባሉ ራዕይ ታየን ወይም መለኮታዊ ሀይል ተሰጠን ፤ ስለዚህ እኛ በሽታችሁን እናዉቅላችኋለን ፣ እናድናችኋለን ፣ ዕጣ ፈንታችሁን እናሳካላችኋለን ፣ ተከተሉን… እያሉ በቤተክርስቲያኗ አጥር ግቢ ዉስጥ ምዕመኗን የማታለልና የመመዝበር ስራ በሰፊዉ እየሰሩ ይገኛል፡፡ ብዙ ምዕመናንም  በዚህ እኩይ ተግባር ተደናቅፈዋል ፣ አዝነዋል ፣ አንብተዋል…፡፡

እነዚህ በስመ አባወች መንፈስ ቅዱስ ተገለጠልን ይበሉ እንጅ እዉነታዉ ከመንፈሳዊዉ አለም የራቁና ለቁሳዊና ለስጋዊ አለም የተገዙ በነዋይ ፍቅር ያበዱ የዘመናችን አታላዮች ሲሆኑ፡፡  በሚደረድሩዋቸዉ የመፃህፍ ቅዱስ ቃላት በመታገዝ ምዕመኑን በማታለል ከአፉ እየመነጨቁ ከፍተኛ ሀብትና ንብረት ለማካበት ሲሯሯጡ ይታያል፡፡ አንዳንዶቹም ትልልቅ ፎቆችና ቪላዎች እስከመገንባትና መኪናዎች እስከመግዛት ደርሰዋል፡፡

እዚህ ላይ በቅርቡ የተደረገን አንድ አሳፋሪ የማጭበርበር ስራ እንደ ምሳሌ ልጥቀስ፡፡ ድርጊቱ የተፈፀመዉ በጎንደር ከተማ ነዉ፡፡ መነኩሴ ነኝ ባዩ ሰዉ የከተማዋ ነዋሪ የሆኑን አንዲት ሴትዮ እጣፈንታሽ ታየኝ እናም እዉን ይሆን ዘንድ ከፆም ከፀሎት ጋር የምልሽን መተግበር ይኖርብሻል ይላሉ፡፡ ሴትዮዋም መንፈሳዊ ቢጤ ነበሩና ፍፁም አመኑት ፤ ዕጣ ፈንታቸዉ እዉን እንዲሆንም በመነኩሴዉ ዉሳኔ መሰረት ሱባኤ ተቀመጡ፡፡ በዚህ መሀል መነኩሴዉ አዲስ ብስራት ነዉ ያሉትን ይዘዉ ይመጣሉ፡- “እግዚአብሔር ባል ልኮልሻል ከሱም ልጅ ትወልጃለሽ ህይወትሽም በሀሴት ትሞላለች… ይላሉ፡፡” ይህ በሆነ በሳምንቱ አንድ ሰዉ እግዚአብሔር ወደ አንች መራኝ በማለት ሴትዮዋን ይተዋወቃል፡፡ የእግዚአብሔር ስራ ነዉ ብለዉ ሰዉየዉን ያመኑት ሴትም ያለማቅማማት የህይወት እጣፈንታቸዉ የተባለዉን ሰዉ በጥድፊያ ያገባሉ፡፡ ሰዉየው ግን የመነኩሴዉ  ግብረ-አበር ነበር፡፡ ከዛማ አባ ያስጎመዣቸዉ የሴትዮዋ የተንጣለለ ቤት ነበርና ከሴትዮዋ ባል ተብየ ጋር በመተባበር ሴትዮዋን አሳምነዉ ቤቱን ከነሙሉ  ዕቃዉ በማሸጥ የራሳቸዉ አደረጉ፡፡ ያም አልበቃ ብሏቸዉ ለሴትዮዋ ከአሜሪካ የተላከን 30‹000 ብር  መነተፉ፡፡ ከግዜ በኃላ የእናቱን መታለል በወሬ የሰማ አንዱ ልጃቸዉ ከአሜሪካ በመምጣት እናቱን የአዕምሮ ህክምና እንዲከታተሉ አደረግ፡፡ ከሁሉም በጣም የሚያስገርመዉ ግን ከዚህ በኋላ የተከሰተዉ ነበር ፤ እናቱ የተነጠቁትን ንብረት ለማስመለስ ወደ ጎንደር ከተማ የሄደዉ ልጅ ከባድ ማስፈራሪያና ዛቻ በአባ ተላላኪወች የተፈፀመበት ሲሆን ፤ ልጁ ለህይወቱ በመስጋቱ ለመመለስ ተገዷል ፤ በኋላም የናቱንም ቋሚ አድራሻ ቀይሯል፡፡

እዚህ ላይ አንድ ተጨማሪ ምሳሌ ልድገም፡፡ ድርጊቱ የተፈፀመዉ በደቡብ ጎንደር ዞን ነዉ፡፡ መነኩሴ ነኝ ባዩ ሰዉ በህልም ተገለጠልኝ በማለት ህዝብን ያሳምናሉ፡፡ ከዚያም ነብይ መጣልን እያለ አገሬዉ መጉረፍ ጀመረ ፤ ገንዘብ ለአባ ከልክ በላይ ዘነበ…ዘነበ…ዘነበ… ፤ ማለቂያ የሌለዉ ገንዘብ በጆንያ ወደ ባንክ ተጋዘና ተከዘነ፡፡ በቃ አባ በእንዲህ ያለ ሁኔታ ህዝቡን በማን አለብኝነት መነተፍ፡፡ ዛሬ እኒህ አባ ተብየ የሚንደላቀቁበት መኪና መግዛት ችለዋል፡፡ ያጡ የነጡ የነበሩት ዘመዶቻቸዉ የናጠጡ ሀብታም ሆነዋል ፤ በአሁኑ ሰዓት በዉቢቷ ባህር ዳር ከተማ እምብርት ትልቅ ዘመናዊ ህንፃ በመገንባት ላይ ይገኛሉ፡፡

እንግዲህ ለምሳሌነት ያህል የነዚህን አባቶች ‹‹ገድል›› ጠቀስኩ እንጅ በሆድ ይፍጀዉ የተዉናቸዉን በርካት መሰል  ታሪኮች መጥቀስ ይቻላል ፤ በርካታ አሳፋሪና አስደንጋጭ  የቀን ዘረፋ በብዙ መንፈሳዊ አባት ነን በሚሉ ሰዎች ተፈፅመዋል፡፡ አሁንም እየተፈፀሙ ይገኛል፡፡

Image
ባለቤትነቱ አንድ ባሕታዊ ነኝ የሚሉ አጭበርብሪ የሆነ በባሕር ዳር ከተማ በግንባታ ላይ የሚገኝ ሕንፃ

እዚህ ላይ በጣም ወደ ሚያሳዝነዉና ወደ ሚያስገርመዉ ጉዳይ ልለፍ ፡፡ የቤተክርስቲያንዋ መሪዎች ይህን መሰል በቤተክርስቲያኗ አጥር ግቢ ዉስጥ በስሟ በምዕመኗ ላይ እየተፈፀመ ያለ ፀያፍ ተግባር እንዴት እየተዋጉ ነዉ ?

በግልፅ እንደሚታወቀዉ  የቤተክርስቲያኗ አመራሮች ቤተክርስቲያንዋን ከጥፋት የመጠበቅ ፣ የመንከባከብ እና  አስተምሮቷንና  ቀኖናዋን ሳይሸራረፍ የማስቀጠል  ሀላፊነት አለባቸዉ ፤ ምዕመኖቿ የተሻለ መንፈሳዊ አገልግሎት እንዲያገኙ ማድረግም ይጠበቅባቸዋል፡፡ ነገር ግን እየሆነ ያለዉን ስንመለከት ከዚህ ፍፁም የተለየ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ ምንም እንኳን ችግሩ ከላይ እንዳየነዉ የከፋና ከግዜ ወደ ግዜ እየተባባሰ የመጣ ቢሆንም መሪዎቹ ግን አይቶ እንዳላየ ሰምቶ እንዳልሰማ መሆንን መርጠዋል ፤ ችግሩ የቤተክርስትያኗን ስም የሚያበላሽ መሰረቷንም የሚያናጋ ቢሆንም እነርሱን ግን ብዙም ያሳሰበ አይመስልም፡፡ ይህም ለቤተክርስቲያኗ የቆመ ተቆርቋሪ አካል አለመኖሩን ፍንትዉ አድርጎ የሚያሳይ ነዉ፡፡

እዚህ ላይ አንድ ነገር ጠቁሜ ሀሳቤን ልቋጭ፡፡  ዛሬ ላይ በቤተክርስቲያኗ ስም በአጥር ግቢዋ እየተፈፀመ ያለዉ ይህ አስነዋሪ ተግባር ለቤተክርስቲያኗ ትልቅ አደጋ ነዉ፡፡  ችግሩ የቤተክርስቲያኗን ስም ከማቆሸሽ ባሻገር ነገ ከነገ-ወዲያ መንፈሳዊ አገልግሎቷንም ጥርጣሬ ላይ ሊጥል ይችላል ፤ ለዘመናት በማህበረሰቡ ዉስጥ የተከበሩና የታፈሩ የነበሩትን መንፈሳዊ አባቶቿን ስም ክፉኛ ያበላሻል፡፡ ስለሆነም  የቤተክርስቲያኗ አመራሮች ከተዘፈቁበት የግዴለሽነት ባህር ወጥተዉ ችግሩን ከጅምሩ ለማስወገድ መንቀሳቀስ አለባቸዉ፡፡ ምዕመናኑም በበኩሉ ለምድ የለበሱ አስመሳይ የተኩላ ባህታዊ እንዳሉ በመገንዘብ እራሱን መጠበቅ ይኖርበታል፡፡

፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡

ከዚህ በላይ ያሰፈርኩት ሀሳብ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ከመጥላት ፣ መንፈሳዊ መሪወቿን ወይም ካህናትን ለማጥላላት እንዲሁም ስርዓቷን ለመኮነን ሳይሆን የቅርብ ግዜ የቤተክርስቲያኗን ተግዳሮቶች በመጠቆም መፍትሄ እንዲያገኙ በማሰብ ነዉ፡፡ ሀሳቤ በቀናነት የመነጨና በጎ አላማ ያነገበ ነዉ፡፡ ትዝብቴን ለመተቸት ማንም ሰዉ ሙሉ መብት ያለዉ ሲሆን እኔም ስህተቴን ለማስተካከል ዝግጁ መሆኔን እገልፃለሁ፡፡

 

 

 

Advertisements

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s