ዝምታ ለምን ?

እዉነቴን ነዉ የምላችሁ “ጠቅላይ ሚኒስተር መለስ ዜናዊ በጠና ታመዉ ሞት አፋፍ ላይ ናቸዉ” የሚለዉን ዜና ከሰማሁበት ሰዓት ጀምሮ መንፈሴ የታወከ ሲሆን ፤ ደርሶ ብሽቅ ማለትም ጀምሬአለሁ፡፡ ልብ ልትሉት የሚገባ ነገር መንፈሴ የታወከዉም ሆነ ደርሼ ብሽቅ የምለዉ እርሳቸዉን ስለምወዳቸዉ ወይም ለእርሳቸዉ ልዩ ክብር ስላለኝ አይደለም፡፡ እንዴት ብዮ እወዳቸዋለሁ ፤ እንዴት ብየ ልዩ ክብር ይኖረኛል ፤ ለምን እዉነት አወራህ ፣ ለምን ለሀገሪቱ ጥሩ ተመኘህ … ብለዉ በምወደዉ ሙያየ ላይ “አሸባሪ” የሚል ስም ለጥፈዉ ስላሳደዱኝ ፤ የሙያ ጓደኞቸን በሐሰት መስክረዉ በአሰቃቂ ሁኔታ በግዞት ስላስቀመጡዋቸዉ…ወይስ ለምን፡፡ ይልቁንም መንፈሴ የታወከዉ ደርሼም ብሽቅ የምለዉ … እርሳቸዉ እንዲህ አልጋ ቁራኛ በሆኑበት ሰዓት የኛ ኢትዮጵያን ዝምታ እንዲሁም የሀገሪቱ መፃኢ እድል ነዉ፡፡

የፍትህ ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ የሆነዉ ጋዜጠኛ ተመስጌን ደሳለኝ የፍትህን ዌብ-ሳይት ጠቅሶ በፌስ-ቡክ ገጹ ባወጣዉ አንድ ፅሁፉ እንደጠቀሰዉ የኢህአዴግ ዋና አመራሮች (የአቶ መለስ ታማኝ ሎሌዎች) ከአራት ተከፋፍለዉ የስልጣን ይገባኛል ፍልሚያዉን ጀምረዉታል፡፡ ፅሑፉ እንደሚያትተዉ አቦይ ስብሃት ነጋ ፣ አዜብ መስፍን እና በረከት ስምኦን ፣ ኦህዴዶች እንዲሁም አለቃ ፀጋዬ በርሄ በተለያዩ ቡድኖች ተሰልፈዉ ለደጋፊዎቻቸዉ እያቀነቀኑ ይገኛል፡፡ እንግዲህ ልብ በሉ! ይህ የተነሳዉ የስልጣን ይገባኛል ክርክር በአንዱ የበላይነት ተጠናቀቀ ማለት ዳግም እኛ ኢትዮጵያዉያን ለሌላ አንባገነንን መሪ አይናችን እያየ ተሰጠን ማለት ሲሆን ፣ የአገዛዙ ጭቆናና ግፍ ባለበት ይቀጥላል ማለት ነዉ ፡፡ እንግዲህ ዝምታዉ ይህ እየሆነ ባለበት ሰዓት ነዉ፡፡

እኔ እንደሚሰማኝ ሰዓቱ ሁሉም ኢትዮጵያዊ እየተካሄደ ያለዉን የአንባገነኖች የስልጣን ሽግግር የምንቃወምበትና ላለፉት 21 አመታት አሳር ያበላንን አገዛዝ በቃ የምንልበት ነዉ ፤ ለነፃነት ፣ ለዲሞክራሲና ለፍትህ ቆርጠን የምንታገልበት ነዉ፡፡ እስቲ አስቡት! እስከ መቼ ነዉ እንዲህ የአንባገነኖች መጫወቻ ሆነን የምንኖረዉ ? እስከ መቼ ነዉ አንዱ አንባገነን ሂዶ ሌላዉ ሲመጣ በዝምታ የምንቀበለዉ ?

እዚህ ላይ አንድ ጠቃሚ ነገር በጉልህ መጥቀስ እፈልጋለሁ ፤ እናንተም በደንብ ልብ ልትሉት ያስፈልጋል፡፡ የጠቅላይ ሚኒስትሩ በጠና መታመም (ምናልባት ነገ ከነገ ወዲያ ሊሞቱም ይችላሉ) የፈጠሩትን አንባገነን አገዛዝ በቀላሉ ለማስወገድ እና የተሻለ የስርዓት ለዉጥ ለማካሔድ ለኛ ኢትዮጵያዉያን ትልቅ እድልን የከፈተ ጥሩ አጋጣሚ ነዉ ፤ ያዉም በቀላሉ የማይገኝ ጥሩ አጋጣሚ፡፡ ለምን? ካሉ ፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ላለፉት 20 አመታት ኢትዮጵያ የምትባል አዲስ አገርን ከታሪክ ጉያ መንጭቀዉ በፈለጉት መንገድ የመሰረቱና የዚህችን አገር የፖለቲካ መዘወሪያ በጫንቃቸው የተሸከሙ ሰዉ ናቸዉ። አገሪቱን ሲመሩ የስልጣን ተቀናቃኝ በፓርቲያቸዉ እንዳይፈጠርባቸዉ በማሰብ ጠንካራ የሚባሉትን አመራሮች በጠቅላላ ሊባል ይችላል ያስወገዱ ሲሆን ፤ የቀሩትንም (አሁን በስልጣን ላይ ያሉትን ለማለት ነዉ) በርቀት የእርሳቸዉን ቃላት እንደ በቀቀን እየደገሙ የሀገሪቱ የፖለቲካ ሹረት ሳይገባቸዉ እንዲከተሉ አድርገዋል፡፡ ስለሆነም የእርሳቸዉ በጠና መታመም/መሞት የኢህአዲግን አቅም ፍፁም ያዳክማል ፤ እንዴዉም በብዙ መልኩ እንደ ድርጅቱ መታመም/መሞት ሊቆጠርም የሚችል ነዉ፡፡ ለዚህም ነዉ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጀሌዎች የእርሳቸዉ በጠና መታመም እንደ ትልቅ ሚስጥር አፍኖ በመያዝ ምንም እንዳልተፈጠረ ለማስመሰል እየሞከሩ ያሉት፡፡

በጠቅላላ ማለት የምፈልገዉ ይህን ታሪካዊ አጋጣሚ በመጠቀም የተሻለ የስርዓት ለዉጥ ለመፍጠር ግዜ ሳያጠፉ መንቀሳቀስ በዝምታ ተሸብቦ ቀጣይ የሚመጣን አፋኝ አንባገነን በቸልታ ከመቀበል የተሻለ ብልህነት ነዉ ነዉ፡፡ ከገባንበት የዝምታ ባህር በመዉጣት ዘር ፣ ሀይማኖት እና ሌላ አገዛዙ የፈጠራቸዉ ልዩነቶች ሳይበግረን በህብረት እጅ ለጅ በመያያዝ አንባገነኑን ስርአት ለመታገል መነሳት አለብን ፤ ይህን ባደረግን ጊዜ ብቻ ነዉ መጭዉን ጊዜ ብሩህና የተሻለ ማድረግ የምንችለዉ፡፡

እንዴት ተቃዉሞአችንን ማሰማት እንችላለን ?

እንደ እኔ እምነት ተቃዉሞአችን በተለያየ መልኩ ሊካሄድ ይችላል፡፡ ምንም እንኳን መንግስት ሰላማዊ ሰልፍ ማድረግን ቢከለክልም ህገ-መንግስታዊ መብታችን ነዉና በድፍረት አደባባይ በመዉጣት ፍፁም ሰላማዊ በሆነ መንገድ የተቃዉሞ ድምፅን በማሰማት ሊሆን ይችላል፡፡ እዚህ ላይ ምናልባት የሙስሊሙ ህብረተሰብ አሁን እየተከተለ ካለዉ የተቃዉሞ እስትራቴጅ ብዙ መልካም ተሞክሮዎችን መዉሰድ እንችላለን፡፡

እርግጥ እንደ ሀገራችን ነባራዊ ሁኔታ ይህን መሰል ህዝባዊ ተቃዉሞዎች እና ቀጣይ ሊመጡ የሚችሉ የስርዓት ሽግግሮች ስናስብ አንዳንድ ስጋቶች ሊያድሩብን ይችላሉ፡፡ ለምሳሌ ያህል መሰል ህዝባዊ እንቅስቃሴወችን እንደ ሽፋን በመጠቀም አንዳንድ የኢትዮጵያን አንድነት የማይፈልጉ ፣ ለስልጣን ጥማቸዉ የቆሙ ፣ በጠባብ ብሔርተኛ አስተሳሰብ የተሰነጉ አካላት… አፍራሽ ስራ ለመስራት ሊሞክሩ ይችላሉ ፤ ይህንንም ተከትሎ የሀገራችንን ደንነት አደጋ ላይ ሊጥሉ ይችላሉ፡፡ ሆኖም ልብ ልንለዉ የሚገባዉ ነገር እንቅስቃሴያችን ብስለት ከታከለበት እንዲሁም ግብፃዊያን ታህሪር ላይ እንዳደረጉት ፍፁም አንድ በመሆን ለአንድ እና አንድ ዓላማ ማለትም ለሁሉም የቆመ ዲሞክራሲያዊ ስርዓት የመገንባት ዓላማ አንግበን እጅ ለእጅ በመያያዝ ከተነሳን ማን ሊያሰናክለን ይቻለዋል ? ማንም !

ከላይ ከጠቀስኩት ሰላማዊ የተቃዉሞ ሰልፍ ባሻገር ሌላም ሰላማዊ የተቃዉሞ እንቅስቃሴዎችንም ማድረግ እንችላለን ፤ እንዴዉም አጣምረን ከተጠቀምንባቸዉ የተሻለ ዉጤት የማምጣት አቅማቸዉ የበለጠ ይጎለብታል፡፡ ለምሳሌ ያህል የሚከተሉትን ሰላማዊ የተቃዉሞ እንቅስቃሴዎችን ልናካሂድ እንችላለን፡-

• የስራ ማቆም አድማ
• የትምህርት ማቆም አድማ
• ለአገዛዙ የሚደረጉ ማንኛዉም ኢኮኖሚያዊና ቲክኒካዊ ድጋፎችን ማቋረጥ
• የተቃዉሞ ምልክቶች የታተሙባቸዉ ቲሸርቶች ፣ ቆቦች ….መልበስ
• ከላይ እስከታች ያሉ የመንግስት ባለስልጣናትን ከማሕበራዊ ሕይወት ማግለል
• የመንግስት ተቋማትን የምርት ዉጤት አለመግዛት እንዲሁም አለመጠቀም
• ግብር መክፈል ማቆም…
• በተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲወች በሚካሄዱ የተቃዉሞ ስብሰባዎች ላይ መሳተፍ
• በተለያዩ የማህበራዊ ድህረ-ገፆች ላይ በሚካሔዱ ዉይይቶች ላይ በንቃት መሳተፍ

By Betre Yacob

Advertisements

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s