የተለመደዉ የአንባገነኖች የስልጣን አለቅም ግብ-ግብ መጨረሻ ፤ ዉርደት ፣ እስርና ሞት

ባደጉትና ዲሞክራሲያዊ ስርዓት መገንባት በቻሉት የምዕራቡ ሀገሮች አንድ የፖለቲካ ፓርቲ ወይም ግለሰብ ሰላማዊ በሆነ የህዝብ ምርጫ ስልጣን ላይ ይወጣል፡፡ ግዳጁን ባጠናቀቀ ግዜ ወይም በወከለዉ ህዝብ ዘንድ አመኔታን ሲያጣ ደግሞ እንደ አወጣጡ ሁሉ ያለ ምንም ጭቅጭቅ ከስልጣኑ ዉልቅ ይላል፡፡ በእነዚህ ሀገራት ከዚህም በተለየ ሁኔታ መሪዎች በሀገር ላይ ከሚጋረጡ ፈተናዎች ጋር በተያያዘ ሀላፊነታችንን መወጣት አልቻልንም ሲሉ ተፈፀሙ ለሚሏቸዉ ስህተቶች ሁሉ ሀላፊነቱን በመዉሰድ ሌላ አቅምና እዉቀት ለሚፈቅድላቸዉ ሰዎች ስልጣናቸዉን አስረክበዉ በሰላምና በፍቅር ከነሙሉ ክብራቸዉ ሹልክ ይላሉ፡፡

አሁን አሁን ይህን መሰል ዲሞክራሲያዊ የስልጣን ሽግግር በብዙ ሀገሮች እየተስፋፋና እየተለመደ የመጣ ሲሆን ፤ እንደ ጋና ባሉ ኃላ ቀር በሚባለዉ የአፍሪካ አህጉር ዉስጥ በሚገኙ ሀገራትም መታየት ጀምሯል፡፡ ሆኖም ያለመታደል ሆኖ ዛሬም ቢሆን በብዙ የአፍሪካ ሀገሮች መሰል ሰላማዊ የስልጣን ሽግግር ፈታኝ ሆኖ ቀጥሏል፡፡ በተለይም እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ሀገራት አሁንም ገዥዎች ወደ ስልጣን የሚወጡትም ሆነ ከስልጣናቸዉ የሚወርዱት በጠመንጅ ብቻ ነዉ፡፡ እዚህ ላይ ባለፉት 50 ዓመታት ዉስጥ በሀገራችን የተካሄዱ የስልጣን ሽግግሮች ለዚህ አይነተኛ ማሳያ ይሆናሉ፡፡
ብዙዉን ግዜ በእንደዚህ ዓይነት በሐይል በታጀበ የስልጣን ሽግግር ወቅት ስልጣናቸዉን የሙጥኝ የሚሉ አንባገነኖች መጨረሻቸዉ ዘግናኝና አሳፋሪ ዉድቀት ነዉ፡፡ ብዙዎቹ በስልጣን ልቀቅ አለቅም ትግሉ ሕይወታቸዉን ሲያጡ የቀሩት ደግሞ ስልጣናቸዉን ሲነጠቁ በስልጣን ዘመናቸዉ በፈፀሙት ግፍ ስም ወደ ግዞት ይወረወራሉ ወይም ከተወለዱባት እናት ሀገራቸዉ ላንዴና ለመጨረሻ ግዜ ተዋርደዉ ይሰደዳሉ ፤ አንዳንዴም ከዚህ የከፋ ነገር ይገጥማቸዋል፡፡

ለምሳሌ ያህል ከቱንዚያ ተነስቶ የአረቡን ዓለም ያዳረሰዉ አሁንም የት ላይ እንደሚቋጭ ያልታወቀዉ የፀደዩ አቢዎትን ተከትሎ ከስልጣናቸዉ በሰላም እንዲወርዱ ሲለመኑ አሻፈረኝ በማለት ከህዝብ ጋር ግብ ግብ የገጠሙትን የኮሎኔል ሙአመር ጋዳፊን መጨረሻ መመልከት ይቻላል፡፡ ጋዳፊ ስልጣን በሰላም አስረክቦ ከነሙሉ ክብሩ ሹልክ ማለት እየቻለ በእብሪት ተወጥሮ አሻፈረኝ በማለቱ ከራሱ አሳፋሪና ወራዳ ሞት ባሻገር የልጆቹን ህይወት እንደ ቅጠል አርግፏል፡፡

በተመሳሳይ ስልጣን በሰላም እንዲያስረክብ ሲጠየቅ እንቢ ሲል የኖረዉ የግብፁ ሙባረክም አረፍ ብሎ ሰላማዊ አየር እየተነፈሰ ጣፋጭ የሆነ ህይወት ከቤተሰቦቹ ጋር በሚያጣጥምበት ዕድሜዉ ተዋርዶ ወደ እስር ቤት የተወረወረ ሲሆን ፤ የእርሱ ጦስ ለልጁም ሊተርፍ ችሏል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ እነሎረንስ ባግቦን ፣ አሊ አብደላ ሳላህን ፣ ቤን አሊንንና ሌላ በርካታ አንባገነኖችን መጥቀስ ይቻላል፡፡
የሀገራችንንም ታሪክ ስንመለከት በአፄ ሐይለ ስላሴና ባለስልጣናቶቻቸዉ እንዲሁም እነሱን ተክተዉ ወደ ስልጣን በመጡት የደርግ ባለስልጣናት ላይ የደረሰዉ ያዉ የተለመደዉ ዉርደት ፣ እስር እና ሞት ነበር፡፡

የኢህአዴግ ባለስልጣናት መጨረሻ ምን ሊሆን ይችላል?

ምንም እንኳን የአንባገነኖች ከስልጣን አንለቅም ግብ ግብ ዉጤቱ ከላይ እንዳየነዉ በጣም የከፋ ቢሆንም የወቅቱ የሀገራችን መሪዎችና ባለስልጣናቱ ትንሽ እንኳን ከታሪክ መማር አቅቷቸዉ የህዝብ የሆነን ስልጣን ሙጭጭ በማለት ወደ ዉድቀት አፋፍ በፍጥነት እየተንደረደሩ ይገኛል፡፡

እንደሚታወቀዉ የኢህአዴግ ባለስልጣናት ከስልጣን ዉረዱ አንወርድም ግብግቡን በ1997 ከተካሄደዉ ሀገር አቀፍ ምርጫ ማግስት ጀምሮ በይፋ የጀመሩት ሲሆን ፤ በተለይም ከቅርብ ግዜ ወዲህ የተቀዋሚ ፓርቲወችን አመራሮች እና አባላትን በማሳደድ የነፃዉን ፕሬስ ዉጤቶች ሙሉ በሙሉ ሊባል በሚችል ሁኔታ በማጥፋትና ጋዜጠኞቻቸዉንም በሐሰት ዉንጀላ በግፍ በማሰር አፈናዉን ከምን ግዜዉም በላይ አጠናክረዉ ቀጥለዋል፡፡

ይህ እየሆነ ባለበት ሁኔታ የኑሮ ፈተና ፣ የፍትህ ማጣት ፣ ጭቆናና እንግልት… የበዛበት ምስኪን ኢትዮጵያዊ ብሶቱ ከቀን ወደ ቀን እየጨመረ መጦ ዛሬ ለመፈንዳት ቋፍ ላይ ይገኛል፡፡ እንግዲህ ይህ በግልፅ የሚያመለክተዉ በስልጣን ላይ የሚገኙ ባለስልጣናት በታሪካችን እንዳየናቸዉ እና በነኮሎኔል ጋዳፊ እንደደረሰዉ ሁሉ የከፋ አወዳደቅ ለመዉደቅ ቀናቸዉን እየቆጠሩ እንደሆነ ነዉ፡፡
በተለይም የህወሓት ጠንሳሽና የኢህአዴግ መስራቹ እንዲሁም ሀገሪቱን ለ21 አመታት በመዳፋ አስገብቶ የገዛዉ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ በህመም ከስልጣኑ ከተገለለበት ቆይቶም ከሞተበት ግዜ ጀምሮ በብሶት ተወጥሮ የኖረዉ ጭቁን ህዝብ ከምግዜዉም በላይ ለለዉጥ የበለጠ በማቆብቆብ ላይ ነዉ፡፡ ይህንንም ተከትሎ የተለያዩ የተቃዋሚ ፓርቲዎች ልዩነታቸዉን ወደ ጎን በመተዉ እየተሰባሰቡና እተጠናከሩ ሲሆን አለማቀፋዊ ጫናዉም በአገዛዙ ላይ እየበረታ ይገኛል፡፡ አገዛዙ ለርካሽ ትርፍ ሲል የፈለሰፈዉ የጎሳ ፖለቲካም ዛሬ የጠቅላይ ሚኒስትሩን ከስልጣን መገለል ተከትሎ በተነሳዉ የስልጣን ሽኩቻ በራሱ በኢህአዴግ ላይ የማይጠግኑት ትልቅ ስንጥቅ እየፈጠረ ነዉ፡፡ ከዚህም በተጨማሪ እንደ ስልጣናቸዉ መከታ በሚቆጥሩት ጦር ዉስጥም ትልቅ ቅሬታ እየተፈጠረ ይገኛል፡፡ እንግዲህ ይህ ሁሉ ተደማምሮ አገዛዙን ከምን ግዜዉም በላይ ከዉድቀት አፋፍ ላይ አድርሶታል፡፡

እንዴዉም የሙስሊሙ ህብረተሰብ መንግስት በእምነታችን ጣልቃ መግባቱን ያቁም ሲል አስፈሪ የሆነ ህዝባዊ ተቃዉሞ ከወዲሁ የጀመረ ሲሆን ፤ ለሌላዉም የህብረተሰብ ክፍልም ጥያቄወቹን በሰላማዊ ተቃዉሞ እንዲጠይቅ ትልቅ ምሳሌ በመሆን ለታላቅ ህዝባዊ ተቃዉሞ በር ከፍቷል፡፡

ሆኖም ፕሮፌሰር መስፍን ወልደ ማሪያም “ለአንዳንድ ሰዎች ቁልቁለት ቁልቁለት መሆኑ የሚታወቃቸዉ ወርደዉ ወርደዉ ወድቀዉ ሲከሰከሱ ነዉ” ሲሉ “አደጋ ያንዣበበበት የአፍሪካ ቀንድ” በሚለዉ መፅሐፋቸዉ እንደፃፉት ሁሉ አገዛዙ ከዉድቀት አፋፍ ላይ ባለበት በአሁኑ ሰዓትም ባለስልጣናቱ ከአጠገባቸዉ የተለዩትን የአገዛዙ ጭንቅላት የነበሩትን ሰዉ በሌላ አንባገነን በመተካት ጭቆናቸዉን ለማስቀጠል ደፋ ቀና በማለት ላይ ይገኛሉ፡፡ በሰከነ አዕምሮ በማሰብ የህዝቡን የስልጣን ልቀቁ ጥያቄ ዲሚክራሲያዊ በሆነ መንገድ በመመለስና ሌላም የህዝቡን ቁጣ ማብረጃ እርምጃዎችን በመዉሰድ ከፊታቸዉ እየመጣ ካለዉ አስፈሪ ሕዝባዊ ማዕበል እንደማምለጥ ፤ እራሳቸዉንና ቤተሰቦቻቸዉን ከሚመጣዉ መዓት እንደማዳን እነሱ ግን በጭፍን አዕምሮአቸዉ ስልጣናቸዉን ሙጭጭ እንዳሉ የማያዋጣ ግብ ግብ ከህዝብ ጋር ይዘዋል፡፡ የዚህ ግብ ግብ መጨረሻም እየየቀረበ ይገኛል፡፡

የኢህአዴግ ባለስልጣናት መጨረሻቸዉን ለማሳመር ምን ማድረግ ይችላሉ ?

የኢህአዴግ ባለስልጣናት ከፊት ለፊታቸዉ እየመጣ ካለዉ የከፋ አወዳደቅ እራሳቸዉን ለማትረፉ 11ኛዉ ሰዓት ላይ ሲሆኑ ፤ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ አሁኑኑ ከተንቀሳቀሱ ከዉድቀቱ ለመዳን አማራጮች አሏቸዉ፡፡ በተያያዙት የጭፍን ጉዞ ከቀጠሉ ግን በቅርቡ እነርሱም በታሪክ እንዳየናቸዉ ግዞት ቤታቸዉ እንግልት ሕይወታቸዉ እንደሚሆን ጥርጥር የለዉም ፤ ሲልም ከዚያ የከፋ ነገር ሊገጥማቸዉም ይችላል፡፡ ከእነዚህ አማራጮች መካከል አሁኑኑ ከዚህ በታች የተዘረዘሩትን እርምጃወች በመዉሰድ ያስከፉትን ህዝብ ማስደሰትና ይቅርታዉን ማግኘት ዋናዉና በጣም ቀላሉ ሲሆን ፤ ይህንን በመፈፀማቸዉ እራሳቸዉንና ቤተሰቦቻቸዉን ከሚመጣባቸዉ ችግር ከማዉጣት ባሻገር ስማቸዉንም በኢትዮጵያ ታሪክ ዉስጥ በበጎ ይፅፋሉ፡፡ በህዝቡም ዘንድ ትልቅ ከበሬታን ይጎናፀፋሉ፡፡

ከእነዚህ የህዝቡን ይቅርታ ለማግኘትና ከበሬታን ለመጎናፀፍ ሊወስዷቸዉ ከሚገቧቸዉ አፋጣኝ እርምጃወች ዉስጥ የሚከተሉት ዋና ዋናዎቹ ናቸዉ፡-

1. ስልጣናቸዉን ለተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች ማጋራትና ጥምር መንግስት መመስረት
2. የፖለቲካ እስረኞችንና ጋዜጠኞችን መፍታት
3. ብሔራዊ እርቅ ማካሔድ
4. በፖለቲካ ችግር ከሀገር የተሰደዱ ኢትዮጵያዉያንን ወደ ሀገራቸዉ እንዲመለሱ ከይቅርታ ጋር መጠየቅ ፡፡

By Betre Yacob

Advertisements

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s