የአለም የሴቶች ቀን ታሪካዊ ዳራ

ከበትረ ያዕቆብ

Imageለአለም አቀፍ የሴቶች ቀን (March 8) መከበር ምክንያት የተጠነሰሰው በ18ተኛው ክፍለ ዘመን አጋማሽ ላይ እንደነበር መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ በ1857 እ.ኤ.አ. በአሜሪካ ኒውዮርክ ከተማ የጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካ ሴት ሰራተኞች የአነስተኛ የደሞዝ ክፍያንና ለጤና ምቹ ያልሆኑ የሥራ ሁኔታዎችን በመቃወም በከተማዋ ዋና ዋና ጐዳናዎች ሠላማዊ ሠልፍ አካሄዱ፡፡

በ19ኛው ክፍለ ዘመን ሴቶች ሰብአዊ መብቶቻቸውን ለማስከበር ተቃውሞ የጀመሩበት ወቅት ነበር፡፡ በኢንዱስትሪ በበለፀጉ አገሮች ዘንድ የሠራተኛው ቁጥር ሥርአተ ጾታዊ ስብጥር በከፍተኛ ደረጃ ሚዛናዊ ያልነበረ ከመሆኑ የተነሣ በአብዛኛው በጣም ትንሽ የሚሆኑት የየኢንዱስትሪው ሴት ሰራተኞች ለ191ዐሩ ታሪካዊ ኮንፈረንሰ ቅድመ ሁኔታ መሟላት ምከንያት ነበሩ፡፡ በተለይም በጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካዎችና በማምረቻ ቦታዎች የሚሰሩ ሴት ስራተኞች ለጤና በማይስማማ የሥራ ቦታ ይመደቡ የነበር ከመሆኑም በላይ እጅግ አነስተኛና የዕለት የኑሮ ሕይወታቸውን ለመምራት በማያስችል ክፍያ ይሠቃዩ ነበር፡፡

በዚህም የተነሣ የሴት ሠራተኞቹና ተባባሪ ወንድ አጋሮቻቸው በሚያደርጉት አመጽ በኢንዱስትሪው እንቅስቃሴ ላይ ተደጋጋሚ የሆነ ኪሣራ መድረሱ እየተባባሰ ሄደ፡፡ የሠራተኛው ማህበራት እየተጠናከረ መምጣት በሌላ በኩል ለሴቶች እንቅስቃሴ አጋዥነቱን እያጐላው መጣ፡፡ በአውሮፖ፣ በታላቋ ብሪታንያ፣ በአሜሪካና በትንሹም ቢሆን በአውስትራሊያ ሴቶች የመምረጥና መመረጥ መብታቸው እንዲከበር የሚመለከታቸውን ሁሉ ማግባባት የጀመሩት በ19ኛው ክፍለ ዘመን ነበር፡፡ ይህ ትግላቸው በሴቶች ዙሪያ ይታዩ የነበሩ ማንኛውም ጭቆናዎች እንዲወገዱ አመላካች ከመሆኑም ሌላ ተጨባጭ ለውጥ እንዲከሰት በር ከፋች ሆነ፡፡

በ19ዐ3 በአሜሪካ የሠራተኞች ማህበራትንና ነፃ የሴቶች ማህበራት የሴቶችን በምርጫ የመሣተፍ መብት በመደገፍ የሴቶችን ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ጥንካሬ እንዲመጣ ለመርዳት የሚያስችል የሴት ሠራተኞች ማህበራት ሊግ ተመሠረተ፡፡

በ19ዐ8 አሜሪካ ውስጥ በየካቲት ወር የመጨረሻው ሳምንት ዕሁድ ቀን የአሜሪካ ሶሻሊስት ሴቶች ሰላማዊ ሠልፍ በማደራጀት ለመጀመሪያ ጊዜ “የሴቶች ቀን” በሚል አከበሩ፡፡ የሠላማዊ ሠልፉ ጥያቄ የምርጫ መብትን የሚመለከት ብቻ ሣይሆን ፖለቲካዊና ኢኰኖሚያዊ መብቶቻቸውንም የማረጋገጥ ጭምር ነበር፡፡ በ19ዐ9 እንደዚሁ በአሜሪካ ወደ 3ዐ,ዐዐዐ የሚጠጉ የጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪ ሴት ሠራተኞች ሠላማዊ ሠልፍ በማደራጀት ለ13 ሣምንታት የቀጠለ የሥራ ማቆም አድማ መቱ፡፡ የዚህ ሠላማዊ ሠልፍ አመጽ የተሻለ ክፍያና ምቹ የሥራ ሁኔታ ጥየቃ ነበር፡፡ በዚህ ጊዜ የተቋቋመው የሴት ሠራተኞች ማህበራት ሊግ አመጹን ለማስተባበርና በአመጹ ምክንያት ለታሠሩ ሴቶች የገንዘብ ድጋፍ በማድረግ እንቅስቀሴውን አግዟል፡፡

በ191ዐ የሴቶች ቀን እንዲከበር በመላዋ የአሜሪካ ግዛቶች በሚኖሩ የሴት ሶሻሊስቶችና ፌሚኒስቶች ዘንድ ተቀባይነትን አገኘ፡፡ በ191ዐ እንደዚሁ በዴኒማርክ ኮፐን ሃገን ከተማ በተደረገው 2ኛው አለም አቀፍ የሴቶች ሶሻሊስት ኮንፈረንሰ ላይ የሴቶች ቀን አለም አቀፍ ተቀባይነት ኖሮት እንዲከበር ከሴት ሠራተኞች ማህበራት ሊግ ተወካዮች ሃሳቡ ቀረበ፡፡ አሜሪካ በሴት ሠራተኞች የትግል እንቅስቃሴ በመመሰጥና የራሷን ድርሻ ለመወጣት በማሰብ በአመት አንድ ቀን የሴቶች ዓለም አቀፍ ቀን ሆኖ በ2ኛው አለም አቀፍ የሶሻሊት የሴቶች ኮንፈረንስ ቀርቦ ከ17 ሀገሮች በመጡ የሠራተኞች ማህበራት፣ የሶሻሊስት ፓርቲዎች፣ የሴት ሠራተኞች ክበብ ተወካዮች ዘንድ ያለምንም ድምጽ ልዩነት ሀሳቡ ተቀባይነት አገኘ፡፡ በኮንፈረንሱ የሴቶች በምርጫ የመሣተፍ መብት ጠቀሜታው ከፍተኛ እንደሆነ እንደገና ተረጋገጠ፡፡

የጀርመኗ ክላራ ዜተኪን እና የሩሲያዋ አሌክሳንድራ ኰሎንታይ የሴቶች በምርጫ የመሣተፍ መብት አስገዳጅና ለብቻው ራሱን ችሎ የሶሻሊስት ፕሮግራም አካል ሆኖ መታየትና መረጋገጥ እንደሚገባ ታግለዋል፡፡ በኮፐን ሀገን ኮንፈረንስ ውሳኔ መሠረት ማርች 19/1911 የሴቶች ቀን ሆኖ በኦስትሪያ፣ በዴኒማርክ፣ በጀርመን እና በሲውዘርላንድ መከበር ጀመረ፡፡ በዚሁ ቀን ከአንድ ሚሊዮን በላይ ሴቶችና ወንዶች በአሉን ያከበሩት ሲሆን መሠረታዊ ጥያቄአቸው በሴቶች የመምረጥ መመረጥ መብት ብቻ ሣይሆን፣ የሙያ ክህሎቶቻቸውን የማጐልበትና ፆታን መሠረት ያደረገ መድልኦና ልዩነት እንዲወገድም መታገል እንዳለባቸው በማመላከት ጭምር ነበር፡፡

በመጀመሪያው የአለም ጦርነት ዋዜማ ወቅት ከ1913-1914 የፖስፊስት እንቅስቃሴ ተግባሩን ማከናወን እንደጀመረ የሩሲያ ሴቶች ለመጀመሪያ ጊዜ በ1913 የካቲት ወር የመጨረሻው ዕሁድ ዕለት የሴቶች ቀንን አከበሩ፡፡ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በአውሮፖ በማንኛውም ቦታ በየአመቱ የማርች 8 ዕለት ወይም በዚሁ ዕለት አካባቢ ጦርነትን በመቃወምም ሆነ ሰላምን በሚሰብክ መንገድ ሲከበር ቆይቷል፡፡

በ1917ቱ የሩሲያ አብዮትና በአንደኛው የዓለም ጦርነት ሳቢያ ከ2 ሚሊዮን በላይ ወታደሮች ከማለቃቸው ጋር ተያይዞ የሩሲያ ሴቶች ጦርነቱ እንዲያበቃ በመቃዎም ጥያቄያቸው “ዳቦና ሰላም” መሆኑን በሰላማዊ ሰልፍ አስተጋቡ፡፡ በጊዜው የሩሲያ ከፍተኛ የፖለቲካ አካል አመጹን ቢቃወምም ሴቶች በአመጹ ከመቀጠል ወደኋላ አላሉም፡፡ ከዚህ አጋጣሚ 4 ቀናት በኋላ የሩሲያ ዛር /መንግስት/ ሥልጣኑን እንዲለቅ አስገዳጅ ሁኔታ በመፈጠሩ ሥልጣኑን ለቀቀ፡፡ በምትኩ ጊዜያዊ ስልጣን የተረከበው አዲሱ መንግስት የሴቶችን የመምረጥ መብት ተቀበለ፡፡ የሴቶች ትግል ሥር እየሰደደና በመላው ዓለም በመስፋፋቱ ለጥያቄአቸው ተገቢ ምላሽ ለማግኘት እልህ አስጨራሽ እንቅስቃሴያቸው ተፋፍሞ ቀጠለ፡፡

አለም አቀፍ የሴቶች ቀን እ.ኤ.አ. ከ1910 ዓ.ም ጀምሮ በተለያዩ ሐገራት መከበር ቢጀምርም በሩሲያ የ1917 አብዮት ወቅት በሴቶች አመጽ አስገዳጅነት መንግስት የሴቶችን መብት የተቀበለበትና በዓሉ የተከበረበት ታሪካዊ የመጨረሻ ቀን የካቲት ዕሁድ የነበረው በ1917 የካቲት 23 እንደ ጃሊያን አቆጣጠር ወይም እንደ ጐርጐሪያን አቆጣጠር ማርች 8 ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ከ3 ዓመታት በኋላ በ1921 ማርች 8 አለም አቀፍ የሴቶች ቀን ይፋ ሆኖ መከበር ጀመረ፡፡ የተጋጋለው የሴቶች ቀን ተፋፍሞ ባለበት በመቀጠል በ1977 እ.ኤ.አ. የተባበሩት መንግስታት ድርጅትም ማርች 8 አለም አቀፍ የሴቶች ቀን ሆኖ እንዲከበር ወሰነ፡፡

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out / Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out / Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out / Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out / Change )

Connecting to %s