በግብጽ ኩዴታ ተካሄደ ቢባል ማን ይከራከራል?

የግብጽ ፕሬዚዳንት ከስልጣን የወረዱበት መንገድ  ወደፊት ግብጽን ዋጋ እነደሚያስከፍላት ፣ ምን አልባትም አደገኛ መተራመስ ውስጥ ሊከታት እንደሚችል የሚጠቁሙ ጉዳዮች ስለመታያታቸው የሚናገሩ አሉ። ግብጽ አገር የሚኖር ጓደኛዬ የሙርሲ ደጋፊዎች በቀላሉ የሚያቆሙ አይሆኑም። ሁሉም ሆኖ ግን በህግ የተመረጠ ፕሬዚዳንት በነውጥ እንዲወርድ ሲደረግ ነጮቹ ምነው ዝም አሉ? የአፍሪካ ህብረት ለታሪክ  ፍጆታ የሚውል ውሳኔ የሚያሳድረው ጫና ባይኖርም ” ነግ በኔ” እንዲሉ ድምጻቸውን ማሰማታቸው በዚህ ጉዳይ ከነጮቹ እንዲሻሉ አድርጓቸዋል። ነጪቹ አውቀው ዝም ቢሉም።

ከሁሉም በላይ የሚገርመው ይሄ ጣሂር አደባባይ የሚባለው ቦታ የሚጎርፈው የሰው ነዶ ነው። ግብጻዊያን ስለ አገራቸው ማሰብ ያቆሙ ይመስላል። የማይፈልጉትን ለመቃወም የሚያደርጉት ትብብር ቢያስደስትም ተቃውሟቸውን የሚገልጹበት አንዳንዱ መንገድ እጅግ ሁዋላ ቀር ነው። በህግና በዴሞክራሲያዊ መንገድ የተመረጡ ፕሬዚዳንት የስራ ጊዜያቸውን ሳያጠናቅቁ ባንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ አደባባይ በወመውጣት መተራመሳቸው አሳዛኝ፣ ሲቆይ የሚለበልብ የሚሆን ይመስለኛል።

ትንሽ ያዝናኑኝ ቀን እቆጠሩ ያሉት የቀድሞው አምባገነን ፕሬዚዳንት ሙባረክ ” ለህዝብ ጥያቄ ስትል ስልጣንህን ልቀቅ” በማለት ሙርሲን መክረዋል ተብሎ መነገሩ ነው። በሌላ በኩል አሜሪካን አገር የሚኖሩ የሙስሊም ወንድማማቾች ህብረት ፓርቲ አባልና አማካሪ ”  አሁንም አለን። ከግብጽ ስርዓትና የፖለቲካ መስመር ልንለይ አንችልም” ሲሉ ለሲኤንኤን መናገራቸው የሽግግሩ መንግስት ” የኩዴታው መንግሰት” ጊዜውን ሲጨርስ ምን ሊሆን እንዲችል ከወዲሁ ለመገመት ያስችግራል። እዚህ ላይ የማኢረሳው፣ ግብጾች ለቀጣዩ ምርጫ ለመሰየም፣  አንደገና ጣሂር አደባባይ ዛሬ ኡ ኡ ብለው ስልጣን የሰጡትን የኩዴታውን መንግስት ለመቃወም መውጣታቸው አይቀርም። ይህንን ባያደርጉ ራሱ አደባባዩ ያዝንባቸዋል።

የግብጽ የጦር ሃይል    48 ሰዓታት በመስጠት አጣድፎ ያሰናበታቸው ፕሬዚዳንት ሙርሲ የታሰሩበት ምክንያትስ ምን ይሆን? መፈንቅለ መንግሰት የተከናወነባቸው፣ በህዝብ ድምጽ በዲሞክራሲያዊ መንገድ ተመርጠው ሳለ ኩዴታ የተፈጸመባቸው እሳቸው ሆነው ሳለ እንዲታሰሩ መደረጉ በራሱ ሴራው ሌላ አጀንዳና ተልዕኮ ያለው ያስመስለዋል። የብራዘርስ ሁድ ፓርቲ ልክ የእድር ያህል በመረዳዳት ላይ የተመሰረተ የረዥም ጊዜ የማህበራዊ ግንኙነት ውጤት እንደሂሆነ የሚናገሩ ክፍሎች ” ይህ ፓርቲ ከቶውንም አሜሪካኖቹ ከፈበረኩት አሸባሪና የአሸባሪነት መረብ ጋር ግንኙነት የለውም” አሸባሪና ሽብር ፈጣሪ የሚባሉት ጉዳዮች በማንና እንዴት ተፈጠሩ የሚለው ጉዳይ ውስጥ ባልገባም፣   ውስን ጥያቄዎች ለማንሳት እወዳለሁ።   “አሸባሪ አለ ወይ?አሸባሪ ማለት ምን ማለት ነው? አሸባሪነትንና የሽብር አለቆች የሚባሉትን ማን ፈጠራቸው? እንዴት ተፈጠሩ? ራሱ ቢንላደን የሚባለው ወሮ በላ በነ ማን ተፈጠረ?” ይገርማል።  አሸባሪ፣ ሽብርና፣ የሽብር ሃሳብ የሚባሉት፣ እንዲሁም “ሽብርን አስቀድሞ ማምከንና መከላከል” የሚባሉትን ቅድመ ሃሳቦች በመንተራስ የፈለጉትን ሰው አገር ድረስ እየዘለቁ የሚፈጽሙት ” እነ ጌቶች” ይህንን “ገጸ ባህሪ፣ አሸባሪነትን” ድርስት ስለመሆኑ …….

ለማንኛውም ዛሬ የድር መረብ ስጎረጉር  Sami Man  በሚል የፌስ ቡክ ስም  ሙርሲ ሆይ እናከብራሐለን‘ በሚል ርዕስ ያገኘሁት ጽሁፍ ለወዳጆቼ አጋራሁ!!

የሙርሲ ነገር እና የአባይ ነገር

የሙርሲ ነገር እና የአባይ ነገር
ከግርማ ደስታ

ለወትሮው ሐቅን በመሸፋፈን የሚታወቀው የአፍሪቃ ህብረት የግብጹን መፈንቅለ መንግስት ያወገዘ ብቸኛ ተቋም ሆኗል። ግብጽንም ከአባልነት አግዷታል። ዜናውን የዘገበው አልጀዚራ ነው። ዛሬ በዚሁ ጣቢያ እንዳየሁት ከሆነ በፕሬዚዳንት ሙሐመድ ሙርሲ ላይ የተነሱ ተቃዋሚዎች ከሙርሲ ደጋፊዎች በጣም ያንሳሉ። ትላንት የጀመረውና ዛሬም የቀጠለው የሙርሲ ደጋፊዎች ህዝባዊ ሰልፍ የዚሁ ነጸብራቅ ነው። ሙርሲ እንደተባለው 20 ሚሊዮን ህዝብ በፊርማው (ፔቲሽን) “ይውረድልን” በማለት ጥላቻውን የገለጸለት መሪ አለመሆኑ ፍንጭ እየታየ ነው። ይህም የጄኔራሎቹን ሆድ ሳያንቦጫቡጭ አልቀረም። ለዚህም ይመስላል ወታደሮቹ ትላንት ያሰሩትን የኢኽዋነል ሙስሊሚን (Muslim Brotherhood) መሪ ዛሬ የለቀቁትና ከሰልፉ ቦታ ሄዶ ደጋፊዎቹን ያበረታታው። አዲሱ ጊዜያዊ ፕሬዚዳንትም በቀኑ መገባደጃ ላይ ባደረጉት ንግግር “ኢኽዋኖች ወንድሞቻችን ናችሁ፣ ኑና አብረን እንስራ” የሚል ጥሪ አቅርበዋል። “ተመሩድ” ከሚባለው የወጣቶች ንቅናቄ ጋር ቁርኝት ያላቸው በርካታ ተቃዋሚ ፖለቲከኞችም ዛሬ ግልብጥ ብለው በገልለተኛት ስልት “አገራችንን ከጥፋት እንጠብቅ፤ የውይይት መስመር እንክፈት” የሚል ሃሳብ በመሰንዘር ላይ ናቸው። ጄኔራሎቹም 300 የኢኽዋነል ሙስሊሚን (Muslim Brotherhood) አባላት ለእስር ይፈለጋሉ ባሉት መሰረት በከፍተኛ ወኔ የጀመሩትን ፓርቲውን የማዳከም ዘመቻ ግማሹን እንኳ ሳይተገብሩ ወደ ኋላ አፈግፍገዋል።

እነዚህ ሁኔታዎች አንድ በአንድ ሲገመገሙ ዕሮብ ዕለት የተካሄደው አብዮት ሳይሆን መፈንቅለ መንግሥት ነው ወደ ሚል መደምደሚያ ይወስዱናል። ጄኔራሎቹ በህዝብ ስም “አብዮት” የሚል ቲያትር እየተጫወቱ ነው። ሰልፈኛ ተጠራርቶ በህግ የተመረጠውን ፕሬዚዳንት ያለበቂ ማስረጃ ከስልጣን አውርዱልን ካለ በግብጽ ጄኔራሎች መዝገበ ቃላት “አብዮት” ይባላል ማለት ነው።

የዲሞክራሲ ጽንሠ ሀሳብ እንደሚያስረዳን በህጋዊ ምርጫ ወደ ስልጣን የመጣ መሪ ከስልጣን የሚወገደው በህዝብ ድምጽ ነው እንጂ በተቃውሞ ሰልፍ አይደለም። ሰውየው ከተሰጠው የጊዜ ገደብ በላይ ልምራ ካለ ያኔ አብዮት መቀስቀስ ህጋዊ ብቻ ሳይሆን የግዴታ መወሰድ ያለበት እርምጃ ነው። ደግሞም መሪው በማስረጃ የተረጋገጠ ከባድ ወንጀል ከተገኘበት ከቦታው ሊፈነገል ይችላል። መሪው ከአግባብ ውጪ ወደ ስልጣን መምጣቱ ከታወቀም መባረሩ ተገቢ ነው (የወተር ጌቱን ቅሌት ያስታውሷል)። አዲሱ የግብጽ “አብዮት” ግን ይህንን መርሆ በግማሽ እንኳ የሚያሟላ አይደለም። ለሙርሲ መባረር የቀረቡት ምክንያቶች “ኢኮኖሚውን አላነቃቃም፤ ስራ አጥነትን አላስወገደም፣ ፖሊሱን መቆጣጠር ስላልቻለ ወንጀለኝነት እየተስፋፋ ነው” የመሳሰሉት ናቸው። ምዕራባዊያንና አንዳንድ ምስራቃዊያን የሙርሲን ፓርቲ ጥላሸት የሚቀቡበት “እስላማዊ መንግሥት የመመስረት ድብቅ አጀንዳ አለው” ዓይነት ክስ እንኳ ከግብጻዊያን በኩል አልተሰማም (ሙርሲን ያስወገዱት ጄኔራሎችም እንዲህ ዓይነት ክስ አላሰሙም)።

ፕሬዚዳንቱ ወደ ስልጣን ከመጣ ገና አንድ ዓመቱ ነው። ይህ መሪ እጅግ በጣም የደነበሸ ኢኮኖሚና የተወለጋገደ ቢሮክራሲ ነው ከሙባረክ አገዛዝ የተረከበው። አሁን በካይሮ ጎዳናዎች ላይ የሚተራመሰውን ስራ አጥ ሰራዊት የወረሰው ካለፈው ስርዓት ነው። በስልጣን ላይ በቆየበት የአንድ ዓመት ጊዜ ሰላም አላገኘም። ሰልፍ፣ ወከባ፣ የፖሊስ እሰጥ አገባ፣ የፓርማላ ብወዛ፣ የፍርድ ቤት ሙግት፣ የጄኔራሎች ጭቅጭቅ፣ የሚኒስትሮች አተካራ፣ የጎዳና ላይ ወንጀል ወዘተ… ቀልቡን ሲያሳጣው ነበር። ሙርሲ ይህንን ሁሉ ንዝንዝ ተቋቁሞ እዚህ መድረሱ በትንሹም ቢሆን ጥንካሬ አለው ያሰኛል። ከዚህ የበለጠ ጥንካሬ ያለው መሆኑ የሚፈተነው የተመደበለትን ጊዜ በአግባቡ እንዲመራ ቢደረግ ነበር። አሁን የቀረቡበት ክሶች እርሱን የሚገልጹት መሆናቸው የሚታወቀውም በስልጣን ዘመኑ መገባደጃ ላይ ነው። ያ ግን አልሆነም። በአንድ ዓመት “ኢኮኖሚውን መለወጥ፣ ወንጀሎችንም ማጥፋት ነበረበት” ነው የተባለው። በሌላ አገላለጽ ዘመናዊቷ ግብጽ (ከንጉሳዊ አገዛዝ ነጻ የወጣችው) በ1952 በጀማል ዐብዱናሲር አማካኝነት ከተበሰረችበት ዘመን ጀምሮ ለ60 ዓመታት ሲንከባለል የቆየን ችግር በአንድ ዓመት ማስወገድ ነበረበት የሚል ግምገማ ነው የቀረበበት። ይህ ግን እኔ በተማርኩት የአዳም ስሚዝ ኢኮኖሚክስም ሆነ ላይ ላዩን ባነበብኩት የሶሻሊስት ኢኮኖሚክስ የማይቻል ብቻ ሳይሆን የማይታሰብም ነው።

ሙርሲ በእርግጥ በዚህ ምክንያት ነው የተባረረው? በዚህ ምክንያት ተባርሮ ከሆነ መቼም አሳዛኝ ትራጄዲ ነው የሚሆነው። ህግን እንዲህ እያዋረዱ ዲሞክራሲን እንገነባለን ማለት በምጸትና በሹፈት ሀገርን መግደል ነው እንጂ ሀገር ማዳን አይደለም። ሁኔታው ባጠቃላይ በህዝብ የተመረጡት የቺሊው ሳልቫዶር አየንዴ በ1970ዎቹ በአጉስቶ ፒኖሼ የተባረሩበትና የተገደሉበትን ትራጂዴ ነው የሚያስታውሰኝ።

የሙርሲ ወሬ የአሳዛኝነቱን ያህል በአስቂኝ ኮሚዲ የታጀበም ሆኗል። ለምሳሌ መፈንቅለ መንግሥቱን ያወደሱትን ሀገራት ቅንብር ተመልከቱ። ቀጠር (ኳታር)፣ ኢማራት፣ ሱዑዲ ዐረቢያ፣ ወዘተ… “ጄኔራሎቹ ትክክል ናቸው! አዲሱ መሪ ሆይ እንኳይ ደስ አለህ” የሚል ንጉሣዊ እወጃ አሰምተዋል። እነዚህ በህልም እንኳ ዲሞክራሲን ለዜጎቻቸው የማይመኙ ሀገራት በግብጽ ጄኔራሎች የተወሰደውን እርምጃ ሲያሞካሹ በኛም ሀገር ተመሳሳይ እርምጃ መወሰድ አለበት የሚል አሽሙር የሚናገሩ ይመስላሉ። የሶሪያው መሪ አባባል ግን ከሁሉም ያስቃል (ያስቃል ብለን እንለፈው)።

ምዕራባዊያኑ የወታደሮቹን እርምጃ አፍ አውጥተው “መፈንቅለ መንግሥት ነው” በማለት ባያወግዙትም በዲፕሎማሲ ቋንቋ “የሲቪል አስተዳደር በቶሎ ይመለስ” የሚል ማሳሰቢያ እየሰጡ ነው። የነርሱ እንኳ ይሻላል፤ ምክንያቱም ከዐረብ ጸደይ (The Arab Spring) ወዲህ የሚታዩት ነገሮች ግራ ሆነውባቸዋልና። በእውነትም በየወቅቱ ከሚያዩዋቸው አዳዲስ ነገሮች የቱን ጨብጠው የቱን እንደሚተው መረዳት ከብዶአቸዋል። ከምርጫው በፊት “ኢኽዋን አክራሪነት የተጸናወተው ነው” ሲሉ ቆይተው ከምርጫው በኋላ የኢኽዋን መሪዎችን ለጉብኝት ወደ ቤተ መንግሥታቸው የጋበዙት ነገሩ ሁሉ እንዲህ ግራ ስለሆነባቸው ነው። ቢሆንም “ወታደር ከፖለቲካ ይውጣ፣ ህዝባዊ ምርጫ በቶሎ ይካሄድ” ማለታቸው “ይህ ብቻ አይበቃም! አካፋን አካፋ በሉት!” የሚል የእልህ ጥያቄ ይቀሰቅስ እንደሆን እንጂ ለሳቅ አይጋብዝም (የሶሪያው መሪ ያስተላለፈው መግለጫ አሁን ድረስ ያስቀኛል)።

አንዳንድ ኢትዮጵያዊያን ሙርሲ በአባይ ላይ ካሳየው አቋም ተነስተው “እንኳን ተገነደሰ” እያሉ ደስታቸውን መግለጻቸውም ሌላው ያስገረመኝ ነገር ነው። ታዲያ የኢትዮጵያዊያኑ “እንኳን ተገነደሰ” ያስገረመኝ ስነ-አመክንዮን በመጣሱ ብቻ እንዳይመስላችሁ! ይህ አግባብ ያልሆነ የደስታ ጮቤ ሀገርን እንደ መደገፍ ተደርጎ የሚጻፍ በመሆኑም ጭምር እንጂ። የሙርሲ አላግባብ መባረር ኢትዮጵያን መደገፍ የሚሆነው በየትኛውም ምሁራዊ እይታ ይሆን? (አንዳንዶች ጭራሽ ከሶስት ቀን በፊት በግብጽ ሲካሄድ የነበረውን እየተከታተሉ በየአስራ አምስት ደቂቃው “እሰይ ሙርሲ..ተመታ.. እሰይ ጄኔራሉ ተናገሩ…እሰይ እገሌ ተሾመ” እያሉ በፌስቡክ ሲጽፉ አይቼ ፈገግ ብያለሁ)።

እኔ በትክክል እንደማምነው የሙርሲ ጉዳይ የአባይ ጉዳይ ሳይሆን የህግና የመርህ ጉዳይ ነው መሆን ያለበት። በምርጫ ወደ ስልጣን የመጣ መሪ የሚወገደው በምርጫ ነው። መሪው ያለ ምርጫ የሚወገደው ከላይ የጠቀስኳቸው ሁኔታዎች የተገኙበት ከሆነ ብቻ ነው (ራሱ ፈልጎ ስልጣን ከለቀቀ፣ ወይንም ዶክተሮች የሰውየው ጤንነት ተዛብቷል የሚል በተጨባጭ ማስረጃ የተደገፈ ምክንያት ካቀረቡ ከመሪነት ሊነሳ ይችላል)። እናም ሙርሲ በአባይ ጉዳይ ላይ በደም ፍላት የተናገረው ነገር በዕለተ ረቡዕ የተካሄደውን መፈንቅለ መንግሥት ለመደገፍና ጮቤ ለመርገጥ የሚያነሳሳ መነሾ የሚሆንበት ሎጂካዊ መንገድ የለም። ያ ሌላ ይህ ሌላ!

ሙርሲ በአባይ ጉዳይ ያሳየው አቋም ከርሱ ብቻ የታየ ተደርጎ መወሰዱም አስገራሚ ነገር እየሆነብኝ ነው (አስገራሚዎቹ በዙ መቼስ)። ከዘመነ ሀይለ ሥላሴ ጀምሮ የግብጽ ፖለቲከኞችም ሆኑ መሪዎቻቸው በአባይ ጉዳይ ላይ ያላቸው አቋም አንድ ዓይነት ነው። ሌላው ቀርቶ ተራው ህዝብ እንኳ “ዐባይ ለግብጽ የተሰጠ የፈጣሪ ስጦታ ነው” በማለት ነው የሚያምነው። በአባይ ጉዳይ ላይ ሙርሲ እስከ አሁን ድረስ ከታዩት የግብጽ መሪዎች እጅግ ለዘብተኛው ሊሆን ይችላል፤ ቢያንስ ጩኸቱን ያሰማው ኢትዮጵያ የዓባይን የፍሰት አቅጣጫ መቀየሯ ይፋ ከሆነ በኋላ ነውና። የርሱ ጩኸት አስገራሚ የሚሆንብን ካለ ከጥቂት ዓመታት በፊት በእኛው ሀገር ስለ አባይ ሲነገር የነበረውን ማስታወስ ሊኖርብን ነው። በኢትዮጵያ መንግሥት ወገን ሆነው በአባይ ጉዳይ ሲደራደሩ የነበሩት ሟቹ ፕሮፌሰር ክንፈ አብርሃምና ስለጉዳዩ አጥንቼአለሁ የሚሉት የታሪክ ምሁሩ ረ/ፕሮፌሰር መድኃኔ ታደሰ ሲጽፉትና ሲናገሩት የነበሩትን መለስ ብላችሁ ብታዩአቸው “አባይ እንዲህ ዓይነት መዘዘኛ ከሆነ ቢቀር ይሻላል” ነው የሚያስብሏችሁ። ሟቹ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊም ከሶስት ዓመታት በፊት “ግብጽ ጫካና ተራራ ሳይኖራት በጫካና ተራራ ውጊያ የሰለጠነ ትልቅ ክፍለ ጦር አላት፤ ያ ክፍለ ጦር ከአባይ ጋር ተያይዞ የሚነሳውን ውዝግብ በወታደራዊ ሀይል ለመፍታት ያዘጋጀችው እንደሆነ እናውቃለን” ብለው (ቃለ ምልልሱን ያነበብኩት በአዲስ አድማስ ጋዜጣ እንደሆነ ትዝ ይለኛል)።

ይህንን ያነበበ ታዛቢ “ታዲያ በዚህ አያያዝህ ሙርሲ ስለ አባይ የተናገረው ትክክል ነው ልትል እንዴ?” የሚል ጥያቄ ሊወረውር ይችላል። የኔ መልስ አሁንም “ያ ሌላ ይህ ሌላ!” የሚል ነው። ሙርሲም ሆነ ማንኛውም ግብጻዊ ኢትዮጵያ በአባይ ላይ ያላትን ተፈጥሮአዊና ህጋዊ መብት ማስቀረትም ሆነ መገደብ አይችልም። ሰፊው የኢትዮጵያ ህዝብ አባይን ለልማቱና ለዕድገቱ የመጠቀም ሙሉ መብት አለው። ይህም የግብጽና የሱዳንን ህዝብ በማይጎዳ መልኩ መሆን አለበት። እኔ በዚህ ሐተታ ለመጠቆም የፈለግኳቸው ዋነኛ ነጥቦች

1/. ሙርሲ ኢ-ፍትሐዊ በሆነ መንገድ ከስልጣን መወገዱ አግባብ አይደለም።
2/. የሙርሲን ከስልጣን መባረር ከአባይ ጉዳይ ጋር ማያያዙ አግባብ አይደለም የሚሉት ናቸው።

አንድ ያስደነቀኝን ነገር ላክልበትና ይህንን ጽሁፍ ላብቃ (ያስገረመኝ አላልኩም)። የግብጽ ጄኔራሎች ካለፉት ጥቂት ዓመታት ወዲህ በእጃቸው ያከማቹት ስልጣን ገደብ የለሽ ነው። በረጅሙ የሙባረክ አገዛዝ ዘመን ጄኔራሎቹ የግብጽን ፖለቲካ የመዘወር ችሎታ የነበራቸው ስለመሆኑ በጭራሽ አልሰማንም። ህዝቡ በሙባረክ ላይ ሲነሳሳ ግን “እኛ ለመንግሥት ታዝዘን በህዝብ ላይ አንተኩስም” አሉና ከመሪያቸው ጉያ ተነጥለው ለብቻቸው ቆሙ። ለሶስት ሳምንታት የተካሄደውን ህዝባዊ መነሳሳት ካዩ በኋላም ሙባረክን አባርረው ወደ ከርቸሌ ላኩት። ህገ መንግስት ተረቀቀ ተባለና ሙሐመድ ሙርሲ ተመረጠ።

የእሁዱን ተቃውሞ ተከትሎም ጄኔራሎቹ እንደገና ብቅ አሉና ሙርሲን “ወይ ቁረጥ! ወይ ውረድ!” አሉት። 48 ስምንት ሰዓታትም ሰጡት። ሙርሲም “እናንተ የምትሉትን ሙሉ በሙሉ ለመፈጸም ባልችልም በአዲስ ሁኔታ አዲስ መንግሥት እመሰርታለሁ” አላቸው። ጄኔራሎቹ በአባባሉ ስላልረኩ ከቦታው አነሱትና ሌላ ምርጫ ይደረጋል አሉ። ይህም “አብዮቱን ለማስመለስ የተካሄደ አብዮት ነው” ተባለ (በርግጥ ሚዲያዎች እስከ አሁን ድረስ “መፈንቅለ መንግሥት” እያሉ ነው የሚጠሩት)። ምርጫው ጄነራሎቹ ባቀዱት መልኩ ተካሄደና ሙሐመድ አል-ባራዳይ ፕሬዚዳንት ሆነ እንበል። በስድስተኛው ወሩ የኢኽዋን አል-ሙስሊሚን (Muslim Brotherhood) ደጋፊዎች ወደ አደባባይ ወጥተው “አል-ባራዳይ ሲ.አይ.ኤ ነው፣ አሁኑኑ ይሰቀል” ቢሉ ጄኔራሎቹ እንደገና ጣልቃ ገብተው “በቃህ! አንተም ወደምትሄድበት ሂድ!” ብለው ሊያባርሩት ነው? ከዚያ አምር ሙሳ ተረኛ ፕሬዚዳንት ሆኖ ወንበር ላይ ቢወጣና ተቃዋሚዎቹ በዓመቱ በአንድ መቶ ሺህ ሰልፈኛ ቢያወግዙት እርሱም ሊባረር ነው? ጄኔራሎቹ ይህንን ሁሉ ሊፈጽሙ ነው? ለመሆኑ ጄኔራሎቹ እንዲህ ዘውድ ጫኝና አንጋሽ ከሆኑ ሀገሩን በመምራት ላይ የነበረው ማን ነበር? ወደፊትስ ማን ሊመራት ነው? ጄኔራሎቹ በሙባረክ ዘመንም እንዲሁ ነበሩ? ይህ ትልቅ ችሎታ እያላቸው ነው ሙባረክ በምርጫ ስም ቲያትር ሲሰራ የነበረው?

ዋ ምስኪኑ የሶሪያ ህዝብ! ምነው የግብጽን ጄኔራሎች ለናንተ ባደረገው! አባትየው (ሓፊዝ አል-አሰድ) ከሰላሳ ዓመታት በፊት 40 ሺህ ሰው በግላጭ ጨፈጨፈ። አሁን ደግሞ ልጅየው ሶስት መቶ ሺህ ህዝብ መጨፍጨፉ ተረጋጋጠ። ሳዳምን ያደባዩትና ጋዳፊን ያንከባለሉት የአሜሪካና የፈረንሳይ ጄቶች ወደናንተ አልደርስ አሉ። ምነው ጄኔራሎቻችሁን አንዴ እንደ ግብጽ ጄኔራሎች “ፓወር” ቢሰጣቸው። ዋ ሶሪያ! ዋ ግብጽ! ዋ ሙርሲ! ዋ እንትና! ወዘተ….

Source: http://yabedew.wordpress.com

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out / Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out / Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out / Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out / Change )

Connecting to %s