“ወደ እናት ሀገራችሁ በመምጣት አዲስ አበባ ላይ በሚካሄደዉ ሰላማዊ ሰልፍ ላይ ተሳተፉ!” ፤ እስክንድር ነጋ

በበትረ ያዕቆብ

በአምባገነኑ የኢህአዴግ መንግስት የሐሰት ዉንጀላ ለእስር የተዳረገዉ ታዋቂዉና ተወዳጁ ጋዜጠኛና የፖለቲካ ተንታኝ እስክንድር ነጋ ዲያስፖራዉ በሀገር ዉስጥ እየተካሄደ ባለዉ ሠላማዊ ትግል ላይ በአካል ተገኝቶ እንዲሳተፍ መልዕክት አስተላለፈ፡፡

የፖለቲካና የህሊና እስረኞችን በአካል ለመጠየቅ ቃሊቲ ለተገኙ ጋዜጠኞች እና የአንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ ሕዝባዊ ንቅናቄ የግብር ሃይል አባላት አደራ ሲል ባስተላለፈዉ መልዕክቱ ከአገር ዉጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያዉያን ቀጣይ በሚካሄዱ የተቃዉሞ ሰልፎች ላይ (በተለይም አዲስ አበባ ከተማ ላይ በቅርቡ ሊካሄድ በታቀደዉ ትልቅ ህዝባዊ የተቃዉሞ ሰልፍ ላይ) በአካል በመገኘት ተሳታፊ መሆን ይገባቸዋል ብሏል፡፡

“ዲያስፖራዉ በአካል ተገኝቶ የሚያደርገዉ ተሳትፎ ትግሉን የበለጠ ያጠናክረዋል” ሲል ለጠያቂዎች የተናገረዉ እስክንድር  ነጋ ፤ አያይዞም “ዲያስፖራዉ ማንኛዉንም መስዋትነት ለመክፈል ዝግጁ ሊሆን ይገባል” ብሏል፡፡ በተጨማሪም በግብፅ አቢዎት የግብፅ ዲያስፖራዎች የነበራቸዉን ቀጥተኛ ተሳትፎና ጉልህ ሚና በዝርዝር በመጥቀስ “እኛ ኢትዮጵያዉያን ከእነርሱ ብዙ ልንማር ይገባል” በማለት ተናግሯል፡፡

እስክንድር ደጋግሞ በቅርቡ አዲስ አበባ ከተማ ላይ ሊካሄድ የታቀደዉ ህዝባዊ የተቃዉሞ ሰልፍ ዲያስፖራዉ ለሀገሩ ያለዉን ቀናኢነት እንዲሁም ለወገኑ ያለዉን ፍቅርና ወገንተኝነት በተግባር የሚያሳይበት ትልቅ አጋጣሚ ነዉ ያለ ሲሆን፡፡ ይህን በመረዳት “በዉጭ ሀገራት የሚኖሩ ሀገር ወዳድ ኢትዮጵያዉያን ከአሁኑ በዚህ ታሪካዊ ክስተት ላይ ለመሳተፍ ሊዘጋጁ ይገባል” ብሏል፡፡

አገራችን ኢትዮጵያ እንደ አገር በመቀጠልና ባለመቀጠል አጣብቂኝ ዉስጥ እንዳለች እና ዜጎችም በጭቆና ፍዳቸዉን እያዩ እንደሚገኝ የጠቆመዉ እስክንድር ነጋ ችግሩን ከስር መሰረቱ ለመቅረፍ የግድ ሰላማዊ ትግል ማካሄድ ያስፈልጋል ሲል ተናግሯል፡፡ አያይዞም “አሁን በአንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ መሪነት “የሚሊዎኖች ድምፅ ለነፃነት” በሚል መሪ ቃል የተጀመረዉ የትግል እንቅስቃሴ ይበል የሚያስብልና የሚያበረታታ ነዉ” ያለ ሲሆን፡፡ “ትግሉ በዚሁ ተጠናክሮ ከቀጠለ እንዲሁም የሁላችንም ተሳትፎ ከታከለበት ያለምንም ጥርጥር ወደ ነፃነት ጎዳና ያደርሰናል” ብሏል፡፡

“አትፍሩ! ለአንባገነኖች ዛቻ ቦታ አትስጡ!” በማለት የተናገረዉ እስክንድር ነጋ “ፍርሐት የጨቋኞች ዋንኛ የአፈና መሳሪያ መሆኑን በመገንዘብ ሁሉም በድፍረት ድል ሊያደርገዉ ይገባል ሲል አብራርቷል፡፡” አያይዞም “መቁሰል ፣ መታሰር እና መንገላታት ሊኖር ይችላል ሆኖም ግን ይህ የምንከፍለዉ መስዋትነት አገር አልባ ከመሆን ያድነናል ፤ የተሻለች አገር ለመገንባት እና ለቀጣዩ ትዉልድ ለማስተላለፍ ይረዳናል” ብሏል፡፡ በመጨረሻም “ወደ እናት ሀገራችሁ በመምጣት አዲስ አበባ ላይ በሚካሄደዉ ሰላማዊ ሰልፍ ላይ ተሳተፉ፡፡” ሲል ከአደራ ጋር ለዲያስፖራዉ ጥሪ አስተላልፏል፡፡

Advertisements

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s