“ኢህአዴግ አንገቱን ታንቋል”

Source: www.goolgule.com

ዓለም ባንክ ርምጃ ለመውሰድ ጫፍ ደርሷል ኢህአዴግ ላይ ቀደም ሲል ሲቀርቡበት ከነበሩት ሪፖርቶች በተለየ ጥቅሞቹ ላይ ያነጣጠሩ አስደንጋጭ መረጃዎች እንደወጡበት ተሰማ። መረጃው የኢህአዴግን አንገት የማነቅ ያህል እንደሚቆጠርና ለተግባራዊነቱ የተንቀሳቀሱትን አካላት “የአስተዋይነት” ትግል ውጤት እንደሆነ ተጠቁሟል…

ኢህአዴግ በህዝብ ስም በብድርና በርዳታ የሚያገኘውን ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ ለፖለቲካ ስራ እንደሚያውለውና ለአፈና ተቋማቱ ማጠናከሪያ እንደሚጠቀምበት የተከሰሰበት ሪፖርት መጠናቀቁን የገለጹት የጎልጉል ታማኝ ምንጮች ናቸው። ምንጮቹ እንዳሉት ሪፖርቱ የቀረበለት የዓለም ባንክ በቅርቡ መረጃውን ተቀብሎ ርምጃ ይወስዳል ተብሎ ይጠበቃል። ኢህአዴግ ርምጃው ተግባራዊ ከመሆኑ በፊት ለማክሸፍ የተለመደውን ሩጫ መጀመሩ ተሰምቷል።

በኢህአዴግ ላይ የቀረበው ሪፖርት የመፍትሄ ሃሳብም ያካተተ እንደሆነ የተናገሩት የጎልጉል ምንጮች፣ የዓለም ባንክ የሥራ አስፈጻሚ ቦርድ ሪፖርቱን ሙሉ በሙሉ እንደሚቀበለውና ይፋ እንደሚያደርገው አስረድተዋል። የምርመራ ዘገባውን ስላጠናውና ስላቀረበው የኢንስፔክሽን ተቋምና የስራ ተሞክሮ በቂ ግንዛቤ ያላቸው እነዚህ ክፍሎች እንደሚሉት የዓለም ባንክ ቦርድ ይህ ተቋም ከዚህ ቀደም በተመሳሳይ ያቀረባቸውን ሪፖርቶች ላለመቀበል አንገራግሮ እንደማያውቅ ያስረዳሉ።

በሚመሩት ህዝብ ላይ ግፍ የሚፈጽሙ መንግስታትና በልማት ስም የሰብዓዊ መብት ጥሰት የሚያካሂዱ አገራት የሚፈጸሙ ወንጀሎችን በስፍራው በመገኘትና መረጃዎችን ከመሠረታቸው ዘልቆ በመመርመር  አጥንቶ ተጠያቂ የሚያደርገው ኢንክሉሲቭ ዴቨሎፕመንት ኢንተርናሽናል Inclusive Development International (IDI) የሚባለው ተቋም ከኢትዮጵያውያኑ ሰለባዎች ውክልና በመውሰድ ስራውን ለማከናወን እንቅስቃሴ መጀመሩን ጎልጉል ምንጮቹን በመጥቀስ መዘገቡ ይታወሳል። ተቋሙም በውክልናው መሰረት ለኢንስፔክሽን ፓናል በዝርዝር የሰለባዎቹን በደል በማተት አሳውቆ ነበር።

ኢህአዴግ በርዳታና በብድር የሚያገኘውን ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ ለፖለቲካ ስራ፣ ለአፈና፣ ለወታደራዊ አቅም ግንባታ፣ ለተለያዩ የአፈና ተቋም ሰራተኞቹ ደሞዝና ህዝብን በመርገጥ ስርዓቱን ለሚንከባከቡ የተለያዩ ጥቅማጥቅሞችን በመክፈል ገንዘቡን ለመጠቀም ከታለመለት ዓላማ ውጪ እንደሚያውለው በበርካታ መረጃዎች ያረጋገጠው የኢንስፔክሽን ቡድን ለዚሁ ስራው ኬንያ፣ ደቡብ ሱዳንና ኢትዮጵያ በቅርቡ አቅንቶ ነበር።

ምርመራው ያስደነገጠው ኢህአዴግ በተለያየ መልኩ ሰለባዎች በደላቸውን እንዳይናገሩ፣ በጥቅም የተደለሉ ሰዎችን በየቦታዎቹ በማዘጋጀትና በማስፈራራት አፈና ማካሄዱን የጎልጉል የመረጃ ምንጮች በወቅቱ ቢያስታውቁም ጎልጉል መረጃውን ለስራው መሳካት ሲባል ይፋ ከማድረግ ተቆጥቧል።

ከቀናት በፊት ሪፖርቱን አጠናቆ ለዓለም ባንክ ቦርድ ያቀረበው የኢንስፔክሽን ቡድን (ፓናል) በማያወላዳ መንገድ ተጽኖ ፈጣሪ ተቋም መሆኑንን ያስረዱት ለስራውና ለተቋሙ ቅርበት ያላቸው ክፍሎች፣ ሪፖርቱን ከቦርዱ አባላት አንዱ እንኳ አልቀበልም ቢሉ ምን ሊከሰት እንደሚችልም አብራርተዋል።

“አንድ ወይም ከአንድ በላይ የቦርድ አባላት የፓናሉን ሪፖርት ውይይት እንዲደረግበት እስካልጠየቁ ድረስ ፓናሉ ባቀረበው መሠረት እንዳለ ይጸድቃል። ከጸደቀም በኋላ ሪፖርቱ በዓለም ባንክ ስም ይፋ ይሆናል። ሪፖርቱ ታምኖበት ይፋ ከሆነ በሪፖርቱ የቀረቡት የመፍትሄ ጭብጦች ተግባራዊ ከማድረግ ውጪ ሌላ አማራጭ የለም። እስካሁን ባለው አሰራር የፓናሉ ሪፖርት ተቃውሞ አጋጥሞት አያውቅም” ሲሉ መልስ ሰጥተዋል።

“ይህ ታላቅ ውጤት የተገኘው በእቅድና አስተውሎ በመራመድ ነው። ወደፊትም በቀጣይ የሚከናወኑ ተግባራቶች አሉ። የአገዛዙን ትምክህትና ማን አለብኝነት የሚያረግቡ፣ ብሎም የሚያተኑ ስራዎች ለመስራት ለተጀመረው ስራ ይህ ውጤት ከፍተኛ መነቃቃት ይሆናል” ሲሉ ጉዳዩን በቅርበት በመከታተል እዚህ ያበቁት ክፍሎች አስረድተዋል።

ጉዳዩ እንዴት እዚህ ደረጃ ደረሰ? ለሚሉት ጥያቄዎችና ኢህአዴግ ስለተከሰሰባቸው ዝርዝር ጉዳዮች  October 12, 2012 አስቀድሞ የዘገበውን  ማጣቀስ አግባብ ሆኖ በመገኘቱ ከዚህ በታች እንዳለ አቅርበነዋል።

ኢህአዴግ በ600 ሚሊዮን ዶላር አጣብቂኝ ውስጥ ገባ!!  ብያኔው ከጸና ኪሣራው በቢሊዮን ዶላር ሊደርስም ይችላል!

ኢህአዴግ ከዓለም ባንክ ያገኘውን 600 ሚሊዮን ዶላርና በተመሳሳይ ፕሮጀክት ወደፊት ሊያገኝ የሚችለውን ከፍተኛ ገንዘብ በተመለከተ አደጋ ውስጥ መውደቁ ተሰማ። ኢንስፔክሽን ፓናል (Inspection Panel – IP) የተሰኘ ተቋም ይፋ ያደረገው መረጃ እንደሚያመለክተው ኢህአዴግ የቀረበበት ውንጀላ ከተረጋገጠ የሚያጣው ገንዘብ በቢሊዮን ዶላር እንደሚደርስ ታውቋል። ይፋ የሆነውን መረጃ አስመልክቶ ከኢህአዴግ ወገን እስካሁን በይፋ የተሰጠ ምላሽ የለም።

ግፍ የሚፈጽሙ መንግስታትን፣ በልማት ስም የሰብዓዊ መብት ጥሰት የሚፈጽሙ ወንጀሎችን መረጃዎችን በስፍራው በመገኘትና ከመሠረቱ ዘልቆ በመግባት አደራጅቶ ተጠያቂ የሚያደርገው ኢንክሉሲቭ ዴቨሎፕመንት ኢንተርናሽናል Inclusive Development International (IDI) ከሰለባዎቹ ውክልና ተሰጥቶታል። ተቋሙም በውክልናው መሰረት ለኢንስፔክሽን ፓናል በዝርዝር የሰለባዎቹን በደል በማተት አሳውቋል።

የኢህአዴግ መከላከያ ሠራዊት የሚያደርሰውን እስራት፣ ግርፋት፣ አስገድዶ መድፈር፣ ከመኖሪያ ቦታ ማፈናቀል፣ የግዳጅ ሰፈራ ወዘተ በማምለጥ ወደ ኬንያ የተሰደዱ የጋምቤላ ነዋሪዎች ይህ ሁሉ ግፍ የሚፈጽምባቸው የኢትዮጵያ መንግሥት በልማት ስም ከዓለም ባንክ በሚያገኘው የዕርዳታ ገንዘብ በመሆኑ ለባንኩ በላኩት የአቤቱታ ደብዳቤ አመልክተዋል።

አቤቱታውን መሠረት በማድረግ የሚደረገው ምርመራ ውጤት ይፋ ሲሆን፣ በሌሎች አገሮች እንደተደረገው በዕርዳታ ስም የሚገኝን ገንዘብ ኢህአዴግ ለፖለቲካ ተግባር መጠቀሙ ሲረጋገጥ፣ በመስከረም ወር መጀመሪያ አካባቢ ከዓለም ባንክ ተፈቅዶ የነበረው 600ሚሊዮን ዶላር ሊከለከል ይችላል፡፡

የዛሬ ዘጠኝ ዓመት አካባቢ በሟቹ ጠ/ሚ/ርና የጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ መለስ ዜናዊ ቀጥተኛ ትዕዛዝ በጋምቤላ ክልል በተለይ የተማሩ ወንዶች ላይ በማተኮር 424 ንጹሐን የአኙዋክ ተወላጆች በተገደሉበት ወቅት በሺዎች የሚቆጠሩት ወደ ጎረቤት አገር ኬንያ መሰደዳቸው ይታወሳል፡፡ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ክልሉ ሰላም የለም፡፡ በየጊዜውም የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ሲካሄዱበት ቆይቷል፡፡ በተለይም ለም የሆነውን እጅግ ሰፋፊ መሬት ለውጪ ባለሃብቶች በሳንቲም በመሸጥ ላይ የሚገኘው የኢህአዴግ አገዛዝ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በቀድሞው የደርግ ዘመን ሲካሄድ ከነበረው ባለፈ መልኩ እጅግ በሚያሰቅቅ ሁኔታ በመንደር ምስረታና አስገድዶ የማስፈር ፖሊሲ ከመኖሪያ ቀዬ የማፈናቀል ተግባራትን እያከናወነ መሆኑን የኦክላንድ ተቋም፣ ሂውማን ራይትስ ዎች፣ … የመሳሰሉ ድርጅቶች ያወጧቸው ዘገባዎች ይጠቁማሉ፡፡

ከ1998ዓም ጀምሮ የመሠረታዊ አገልግሎት ጥበቃ ፕሮግራም (Protection of Basic Services “PBS Program”) በሚል በአራት ተከታታይና ሁለት ተጨማሪ የገንዘብ ድጎማ የሚደረግባቸውን ፕሮግራሞች የዓለም ባንክ በኢትዮጵያ ሲያካሂድ ቆይቷል፡፡ ይህ መሠረታዊ የሆኑ አገልግሎቶችን ለማሟላት ተወጥኖ የሚካሄድ ፕሮጀክት በትምህርት፣ በጤና፣ በእርሻ፣ በንጹህ ውሃ አቅርቦት፣ በገጠር መንገድ ሥራ፣ ወዘተ መስኮች ላይ እንዲውል (PBS I, PBS I-AF (Additional Financing), PBS II, PBS 11-AF, PBS-Social Accountability Program and PBS III) በማለት በተለያዩ ደረጃዎች ለተከፋፈለው ኦፐሬሽን ማስፈጸሚያ የሚውለው ገንዘብ ከ13ቢሊዮን ዶላር የሚበልጥ ነው፡፡ ከዚህ ውስጥ ከፍተኛው የዓለም ባንክ ድርሻ 2ቢሊዮን ዶላር ሲሆን የተቀረው በሌሎች ለጋሽ መንግሥታት እና ድርጅቶች የሚሸፈን ነው፡፡ PBS III የተሰኘውን በሦስት ንዑሳን ፕሮግራሞች የተከፋፈለውን ፕሮጀክት ለማስፈጸም በአጠቃላይ የሚፈጀው 6.3ቢሊዮን ዶላር በላይ ነው፡፡ ከዚህ ውስጥ የባንኩ ድርሻ የሆነውን 600ሚሊዮን ዶላር ቦርዱ መስከረም 5ቀን 2005ዓም አጽድቋል፡፡

በአስገድዶ ማስፈር፣ መንደር ምስረታና ሌሎች በርካታ የሰብዓዊ መብቶቻቸው የተጣሱባቸው በኬንያ የሚገኙ ሦስት የአኙዋክ ስደተኞች ተወካይ ድርጅቶች በሰሜን አሜሪካ ከሚገኙ ሌሎች የሰብዓዊ ድርጅቶች ጋር በመሆን ባንኩ ሊሰጥ የወሰነውን ገንዘብ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ጥቅም ከመዋል ይልቅ ለኢህአዴግ የፖለቲካ ዓላማ ማስፈጸሚያ እየዋለ መሆኑን በመጥቀስ ለባንኩ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ጂም ዮንግ ኪም መስከረም 6፤ 2005ዓም ደብዳቤ ልከዋል፡፡ በጥያቄያቸውም መሠረት በዓለም ባንክ በኩል ወደ ኢትዮጵያ የሚፈሰው ገንዘብ “በልማት ስም የኢትዮጵያ መንግሥት በጋምቤላ ክልል ለሚያካሂደው የመንደር ምስረታ እየዋለ ነው” በማለት ይከሳል፡፡ ሲቀጥልም የአኙዋክ ሕዝብ ለዘመናት ከኖረበት መንደር በማፈናቀል “የተሻለ አገልግሎት ይሰጣችኋል” በማለት በግድ የማስፈር ተግባር እየተፈጸመ ሲሆን “የተባለው አገልግሎትም ሆነ ለእርሻ የሚሆን በቂ ቦታ እንዲሁም ለከብቶች የሚበቃ የግጦሽና የውሃ ቦታ የላቸውም” በማለት ሰፈራውን የተቃወሙ ሁሉ እጅግ ከፍተኛ የሆነ የሰብዓዊ መብት ረገጣ እየደረሰባቸው እንደሚገኝ ጠቁሟል፡፡ ይህንን ግፍ የሚፈጽሙት ደግሞ የዓለም ባንክ ለመሠረታዊ አገልግሎት ጥበቃ ፕሮግራም (Protection of Basic Services “PBS Program”) ስም ለልማት እንዲውል ከሚሰጠው የዕርዳታ ገንዘብ በመንግሥት ተቀጥረው ደመወዝ የሚከፈላቸው ሠራተኞች መሆናቸውን ገልጾዋል፡፡ ይህንን ጉዳይ ከዓለም ባንክ ጋር እንዲነጋገሩላቸው Inclusive Development International (IDI) የተባለውን ድርጅት መወከላቸውን አስታውቀዋል፡፡ (የደብዳቤው ሙሉ ቃል እዚህ ላይ ይገኛል)

ተመሳሳይ ጉዳዮችን በዓለምአቀፍ ደረጃ በመከታተልና በማስፈጸም የታወቀው IDI በመስከረም ወር አጋማሽ ላይ ጉዳዩ በቀጥታ ለሚመለከተው የመልሶ ማቋቋምና ልማት ዓለምአቀፍ ባንክና (International Bank for Reconstruction and Development (IBRD)) የዓለምአቀፍ ልማት ማኅበር (International Development Association (IDA)) ሥር ለሚገኘው የኢንስፔክተር ፓናል ባለ 18ገጽ ደብዳቤ ጽፏል፡፡ (የደብዳቤው ሙሉ ቃል እዚህ ላይ ይገኛል) ይህ የኢንስፔክተር ቡድን ከፍተኛ ሥልጣን ያለው መ/ቤት ሲሆን የዓለም ባንክ የሚሰጠውን ገንዘብ በትክክለኛ ቦታ ላይ አለመዋሉን በመጥቀስ ክስ የሚያቀርቡ ወገኖችን ጉዳይ በመከታተልና ቦታው ድረስ የራሱን ምርመራ በማካሄድ ውጤቱ ተግባራዊ እንዲሆን የባንኩን እጅ የማስጠምዘዝ ዓቅም ያለው እንደሆነ ከዚህ በፊት ያካሄዳቸው የምርመራ ውጤቶች ይጠቁማሉ፡፡

ይህ የመርማሪ ቡድን የቀረበለትን አቤቱታ መቀበሉንና በጉዳዩ ላይ የማንም ተጽዕኖ የማይደረግበትን የራሱን ምርመራ እንደሚያደርግ ከትላንት በስቲያ ባወጣው ባለ 8ገጽ መግለጫ ላይ አሳውቋል፡፡ ይህ የአቤቱታ ፋይል ቁጥር የተሰጠው ጉዳይ በግልባጭ ለባንኩ ፕሬዚዳንትና ለከሳሽ ተወካይ ድርጅት (IDI) እንዲደርስ ተደርጓል፡፡(የደብዳቤው ሙሉ ቃል እዚህ ላይ ይገኛል)

የሰሜን አሜሪካ ዘጋቢ ባጠናከረው መረጃ መሠረት ቡድኑ ከያዝነው ዓመት የጥቅምት አጋማሽ በኋላ ወደ ምስራቅ አፍሪካ ያቀናል። ቡድኑ ስደተኞቹ የሚገኙባቸውን፣ እንዲሁም ጉዳዩን በሚመለከት አስፈላጊ የሚላቸውን ቦታዎችና ግለሰቦች ሙሉ በሙሉ ያነጋግራል። ለስራው መሳካት የሚሆነውን ሁሉ በሚፈለግበት ቦታ በመገኘት በግንባር እንደሚያከናውን ለማወቅ ተችሏል።

በተለያየ ጊዜ ኢህአዴግ የሚፈጽመውን ግፍና በደል በማደራጀት ሥርዓቱ ላይ ከትጥቅ የጠነከረ ትግል ማካሄድ እንደሚቻል አስተያየት ሰጪዎች ተናግረዋል:: አያይዘውም በመላው አገሪቱ የሚፈጸመውን የሰብአዊ መብት ረገጣና የመብት ጥሰት በማሰባሰብ የኢህአዴግን የገንዘብ ምንጭ የማድረቅ፣ ብሎም በእርዳታ ገንዘብ የሚገነባቸውን የአፈና ተቋማት ማስለል እንደሚቻል አስታውቀዋል። ይህንን ታላቅ ስራ የሰሩትን አካላት ልምዳቸውን ለሌሎች በማካፈል አስፈላጊውን ስራ ሊሰሩ እንደሚገባም አሳስበዋል።

Advertisements

4 comments

 1. Please please please please the news is originally from goolgule.com It would be great if you are willing to take a correction. 

  Sent from Samsung Mobile

  • Dear Golgul, I am sorry for the problem. I found the news on
   ETHIOANDENT that is why I didn’t mention you.
   From now on I will never make such a mistake. Now I am going to
   correct the source.

  • Dear Golgul, I would like to tell you that the problem didnt happen
   intentionally. I am not a person to stale a property of others.I an
   sorry. Any way I ask you to tell me the titles of the articles I didnt
   mention the source correctly.
   I hope you understand me.
   Thanks a lot!

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s