ሕወሐትና እግሪሐሪባ (የመንግስት የፖሊስ ኮማንደር ለአብርሃ ደስታ ፅፎ የላከለት)

ዛሬ ቢሮ ውስጥ የሰማሁት ነገር ትንሽ አልታኘክ አልዋጥ አለኝ:: የምንሰራበት መስርያ ቤት አንድ ጥግ ላይ አራት የስራ ባልደረቦቼ ‘’የፈለጉትን መሆን አይችሉም እንዴ?’’ ምንድን ነው ነገሩ ፤ እቺ ሃገር ወዴት እዬሄደች ነው ምናንም ምንምን እያሉ ሲያወሩ ሰማኋቸው:: ምን ሁናቹሁ ነው? ብዬ ጠየቅኳቸው:: ከመቀለ ወደ 10ኪሜ ራቅ ብላ የምትገኝ ገጠር አለች ፤ ሰዎቹ በግድ ወደ ከተማ ግቡ ተባሉ ‘አንገባም ሕጋዊ መንገድ አይደለም አካሄዱ’ ብለው ሲከራከሩ አንድ ከክልል ቢሮ የመጣ ባለስልጣን ሳትወዱ ትገባላቹሁ ብሎ ስላስፈራራቸው እነሱም እንግድያውስ ዓረና እንሆናለን በማለት ስብሰባውን ረግጠው በመውጣታቸው የተለያዩ ምክንያት በማቅረብ አስተባባሪዎቹን እያሰሯቸው ነው አሉኝ:: እኔም ጉዳዩ ስላሳዘነኝ መረጃ ለመሰብሰብ ወደ መንደሯ አከባቢ ያሉ ሻሂ ቤቶች በመሄድ አጥጋቢ መረጃ ይዠ መጣሁ ፤ እንሆ::በሕወሐትና በአርሳዶሮች የተሞላች እግሪሐሪባ የሚጣሉቧት በጣም ትንሽዬ መንደር ከመቀሌ ከተማ ጠረፍ የ5ኪሜ ርቀት ያላት ኮረብታማ ገጠር ናት:: እቺ የገጠር መንደር ወይናደጋ የሚባል የአየር ንብረት ያላት ሲሆን ሙሉ በሙሉ በግብርና ራሷን ችላ የምትተዳደር የገጠር መንደር ነች:: እግሪሐሪባ መንደሯ ብቻ 25ስ.ኪሜ የመሬት ስፋት ላይ የምተገኝ ስትሆን እስከ ሶስት ሺ ህዝብ እንደሚኖሩባት ይገመታል:: እግሪሐሪባ አሸጎዳ የንፋስ ሃይል የተባለው ፕሮጀክት በወገቧ እያለፈ መብራት ያላገኘች ሚስኪን መንደር ነቸ!

እግሪሐሪባ ከግዙፉ የሕወሐት መንግስት ጋር በቀልድ የጀመሩት እሰጣ እገባ ወደ ማሰርና መታሰር ገብተው እርፍ አሉ:: ግን እንዴት የህዝብ ወኪሎች ተብለው ቤተመንግስት ተሰብስበው በጅመላ ተጃጅለው እግሪሐሪባዎቹን መጨቆን ይያያዙትታል? አመራር ሙሉ ግን በጅምላ ይጃጃላል እንዴ? አንድ አባል እንኳ ‘አረ ከመጃጃል ዓለም እንውጣ አይልም’? ሕወሐቶች እንዴት ተጃጃሉ ማለት ጥሩ—- ሕወሐቶች የመሬት ወረራቸውን ለማጠናከር እያደረጉት ባሉት ዜዴ አንደኛው ስትራቴጂያቸው መንግስት የማያውቃቹሁ ሰፋሪዎች ናቹሁ በማለት መኖርያቸውን ይነጥቋቸዋል ፤ ባለፉት አራት ተከታታይ ምርጫ በነበረበት ሰዓት ግን መንግስት እንዲመርጣቸው የምርጫ ኮረጆ ወዳሉበት ቦታ ወስዶ እውቅና ሲሰጣቸው ነበር::

ሁለተኛው ደግሞ ለከተማ ቅርብ ስለሆናቹሁ ከተማ መግባት አለባቹሁ ብሎ የመኖርያ ቤታቸውንና ለእርሻ የሚጠቀሙበትን መሬታቸውን ይወስዳል:: ለምን ሲባል ‘ሕወሐትኮ የከተማ እርሻ አትደግፍም’ ብለው የብልሃርዝያ የሚመስል ሕመም ይለቅባቸዋል:: አሁንም ለምን ሲባል ‘’ይሄ ሕወሐቲዝም’’ ይባላል ብሎው እርፍ:: ውይ ‘ሕወሐት ግን መቃብሯ ይቆፈራል’! እግሪሐሪባ ለከተማ ቅርብ ስለሆንሽ ዩኒቨርሲቲም አጠገብሽ ስለተሰራ ከመቀለ ከተማ ጋር መጠቃለል አለብሽ ተባለች:: እምቢ አልጠቀለልም ፤ እንደድሮዬ ራሴን በራሴ እያስተዳደርኩ መቀለን ከሩቅ ማየት ነው የምፈልገው:: ‘እምቢ እንደ መቀለ ማበድ አልፈልግም’ ብላ በወኪሎቿ ስተናገር ሕወሐትዬ ደግሞ እየደጋገመች ሸምጋይ በሌላ ግዜ ደግሞ ገላጋይ ብትልክ እግሪሐሪባዎች ግን አሁንም ‘እምቢ እኛ የብላታ ሃይለማርያም ልጆች’ እምቢ እያሉ ፉከራና ሽለላ የተሞላው መልስ ለሕወሐትዬ ላኩላት::

የቀዳማይ ወያኔ ጠንሳሽ የሆኑት ብላታ ሃይለማርያም አገር ከእግሪሐሪባ 1 ኪሜ ርቀት ያላት ሲሆን ያኔ ብላታ ሃይለማርያም ቀዳማይ ወያኔ ሲጀምሩ እግሪሐሪባዎችን ነበር አሉ ያማከሯቸውም ጃንሆይን ለመድፈር—ያው እዛው አከባቢ የሰማሁትን ነው እንግዲህ እየተናገርኩ ያለሁት:: ሕወሐቶች የእግሪሐሪባ አቋም አስደንግጧቸው በቃ መከተም ካልፈለጉ ተዋቸው ብለው ጉደሰዩን ቸል ሲሉት አንዲት እጅግ በጣም ትንሽ ወደ መቀለ መግባቷ በፀጋ የተቀበለች መንደር ‘’አንጃ’’ ሆና ተነሳች::  አንቺ ደግሞ ምን ሆነሽ ነው? ስተባል —እግሪሐሪባ ከተማ ካልገባችማ እኛም መቀለ መግባት አንፈልግም ፤ እንዴት እናታችን በረሃ ትተን እኛ ከተማ ውስጠ እንሽሎከለካለን ብለው በሙሉ ድምፅ በመናገር መንደሯን የደመራ በዓል አስመሰሏት::

ሕወሐት ካድሬዎቿን ወደ እግሪሐሪባ በመላክ ከተማ ገብታቹሃል ተቀበሉ አሏቸው—-እግሪሐሪባዎች ደግሞ አልገባንም አንገባምም ብለው አስረግጠው ተናገሩ:: ሕወሐትዬ እነዛ የረድኤት እጦት ብሶት የወለዳቸው ሚኒሻዎች በመላክ የእግሪሐሪባ ህዝብ አስተባባሪዎችን በጅምላ አስራ ወደ መቀለ አምጥታ እንደ ነብስ ገዳይ ክስ ሳይመሰረትባቸው ወደ እስር ቤት አስገበታ ‘’አሁንስ ትገባላቹሁ አትገቡም አለቻቸው’’ ታሳሪዎቹም እኛንማ በግድ አስራቹሁ ወደ ከተማ አስገባቹሁን እኮ እግሪሐሪባ ብቻ ነች አዛው ገጠር የቀረችው እንጂ በማለት ቀለዷት:: እስረኞቹ ይህን ሲናገሩ ሕወሐት ተበሳጭታ የስድብ ናዳ አርከፈከፈችባቸው– እናንተ የፊውዳል ልጆች ፤ የመሳፍንት ስርዓት ለማምጣት ነው አይደል ሁከት እየፈጠራቸሁ ያላቹሁት ፤ ቆይ እንተያያለን::

ሕወሐት ትንሽ ቆይታ ደግሞ ‘’አረ ተው እግሪሐሪባዎች ተው ግፍ ነው ፤ የሕወሐት ቃል አንቀበልም የሚባልበት ግዜ እንድረስ ፤ ቱ እያለች አርሶ አደሮችን መለመን ትጀምራለች:: እግሪሐሪባዎቹ ግን ወላ በዱላ ወላ በልመና መከተም አንፈልግም አሉ:: እንዴት የሰው ልጅን በግድ ከትም ይባላል? አንከትምም ፤ ከተማ ከሆንክ የመንግስት አገልጋይ ነው የምትሆነው ገጠር ውስጥ ግን ወላ ፀሎትህ ፥ ወላ ወሬህ ፥ ወላ መሰዳደብህ ፥ ወላ ጠቅላላ ግንኝነታችን ከመሬት ጋር ነው –እ—ደርግ ትግራይን ሲለቅ እኮ ምንም አልሆንም መሬታችን ይዘን ምን እንዳንሆን ነው እያሉ እነዛ የኑሮ ብሶት የወለዳቸውን ካድሬዎች ልክልካቸውን ነገሯቸው::

የእግሪሐሪባ ህዝብ መሪዎቻችን ለምን ይታሰራሉ ፤ እነሱ የተለየ ነገር ምን አደረጉ ይፈቱልን ወይም እኛንም እሰሩን ብሎ ፖሊስ ጣብያውን ወረሩት ልክ ባለፈው አዲስ አበባ አራት ኪሎን አንበጣ እንደወረረው:: ያው እንደሚታወቀው መጀመርያ ህዝቡን ለመበተን ሕወሐትዬ ትግርኛ የሚናገሩ ፖሊሶች ሰደደችላቸው:: ህዝቡ ፖሊሶቹን ናቃቸው…ማን ለማን ቱ ደግሞ የእገሌ ልጅ እኛን ልታስፈራራ አንተ አመዳም ራሳችን አሳድገን… አንተም እኛን ልታዝ ለመሆኑ ማን ነበር ፖሊስ እንድትቀጠር ያደረገህ…ቀጤማ በውሃ አድጋ ውሃን አላሳልፍ አለቻት ነው ነገሩ እያሉ ፖሊሶቹን አሸማቀቋቸው:: አንተ የእገሌ ልጅ ወንድሞችህን እንዳታስፈታ እኛን ልትመታ መጣህ አያሉ ክልላዊ ፖሊሶችን ሆዳቸውን በመብላት ፖሊሶችም ይቅርብን ከህዝባችን ጋር እንዳታነካኩን በማለት ህዝቡን ሳይነኩት ይቀራሉ::

የፖሊስ ሐላፊው ኮማንደር ህዝቡን ሰብስቦ እንዴት ነው ነገሩ ለስምንት ሰው ዋስ ሆኖ ለማስፈታት እኮ ስምንት ሰው ነው የሚያስፈልገው ፤ ለምን ይህን ቦታ ለቃቹሁ አትሄዱም አላቸው:: ህዝቡም ለህዝብ ችግር በመናገራቸው ስለታሰሩ ጠቅላላ ህዝቡ ነው የሚያስፈታቸው ሲሉት ኮማንደሩን ፤ ኮማንደሩ እህህህ እንደዚህ ነው እንዴ ነገሩ ብሎ ወደ ቢሮው ገብቶ ስልኩን ጫን ጫን አድርጎ ሄሎ አለ:: በሃያ ደቂቃ ውስጥ የት እንደነበሩ የማይታወቅ ሶስት ኦራል መኪና የፈደራል ፖሊስ ሰራዊት የያዙ ከች አሉ:: ሕወሐት ከትግርኛ ውጭ ሌላ ቋንቋ የሚናገሩ ፖሊሶች በገዛ ህዝቧ ላይ አሰማራች:: ቋንቋው አማርኛ ነው ፥ ኦሮምኛ ነው ፥ ጋምቤልኛ ነው ፥ ሶማልኛ ነው ፥ ቤኒሽኛ ነው ፥ ወዘተኛ ነው አይታወቅም ፤ ህዝቡ ግን ቋንቋው ራሱ ብትር ሆነበት:: ቀልድ አላውቄዎቹ ፈደራል ፖሊስ በቀጥታ ወደ ህዝቡ በመሄድ ተበ…ተን ብቻ የምትለውን ቃል እያሰማ እናቶችን ከነዘንቢላቸው በጠረባ ይላቸውል ፤ ከዛ እናቶች ወደ ምዕራብ ዘንቢላቸው ወደ ምስራቅ ይወድቃሉ! አባቶችን ደግሞ ከነብትሮቻቸው በጠረባ ፤ አባቶች ከነብትራቸው ወደ መሬት ዘጭ:: ወጣቶችን ደግሞ ምርጫ ይሰጧቸው ነበር ፤ ዱላ ይሻልሃል ወይስ ጠረባ ይሏቸውና መልስ ካልሰጡ አንድላይ ዱላና ጠረባ ያስተናግዳሉ::

ህዝቡ በጣም ደነገጠ—-ሰው የሚመስል እንስሳ አለንዴ እያሉ እርስ በርስ መተያየት ተያያዙት! ሴቶቹ ደግሞ ደርግ መጣ : ደርግ መጣ እያሉ መጮህ ጀመሩ:: ሌሎቹ ደግሞ ታድያ ደርግ እኮ መሬት አይነጥቅም አማርኛ ብቻ ነበር የሚናገረውም ፤ እነዚህ ግን ሻዕብያ እንዳይሆኑ ሻዕብያ ጨካን ስለሆነ ቋንቋ የሌለው አደረጉት:: ህዝቡ በተከታታይ ጠረባ ፥ ቡጤ ፥ ዱላና ምራቅ መትፋት ሲያርፍበት ደንግጦ ፖሊስ ጣብያውን ትቶ ብትንትን አለ:: ፖሊስ ጣብያው አከባቢ ህዝቡ ጥሎት የሄደ የዘንቢል መዓት ፥ የእናቶች የነጠላ መዓት ፥ የአባቶች የብትርና የጋቢ መዓት ለጉድ ነበር:: ፈደራል ፖሊስ ደግሞ የወደቀውን ነጠላ ፥ በትር ፥ ጋቢና ዘንቢል ሰብስቦ ልክ በጦር ሜዳ ላይ ከጠላት የተወረረ ንብረት በማስመሰል ለመንግስት በማሳወቅ ገቢ አደረጉ :: ከሁለት ሳምንት በኋላ እንደ ምንም እስረኞቹ በዋስ ተፈቱና ወደ እግሪሐሪባ ወድያው በመሄድ የፖለቲካ ሰራተኞን/ካድሬዎች/ የግብርና ሰራተኞች ውጡልን ብለው አስወጧቸው:: በመቀጠልም ልጆቻቸውን ትምህርት ቤት አንሰድም አሉና እርሻ ላይ እንዲሰማሩ አደረጉ:: ልጆቻቸሁን እንኳ ወደ ትምህርት ላኩ በነሱ ሂወት መጫወት ነው ሲባሉ ያልላክንበት ምክንያት አለን አሉ ፤ ‘’ካሁን በፊት ልጆቹን ሲያስተምሩ የነበሩ የገጠል ልጆች ነበሩ አሁን መንግስት ጋር ስንጣላ ግን እንዳለ አስተማሪዎቹን በማይታወቁ ቀየርዏቸው:: ካድሬዎች ናቸው ከልጆቻችን ወሬ ለመልቀም ነው የተላኩት:: ነባሮቹ ይመለሱና ልጆቻችን እንልካለን ብለው ተናገሩ::

በእግሪሐሪባ ሶስተ ሺ ህዝብ የላትና በሕወሐት ዘጠና አራት ሚልዮን የሚያስተዳድር ገዢ ፍልምያው ሶስት ዓመት አደረገ:: ሕወሐት ሸምጋይ ብትልክ ገላጋይ ብትልክ እግሪሐሪባዎች ‘’ገጠርነቴ ወይም ሞት’’ ብለው አቋሟቸው ላይ ፀኑ:: ያው እንደሚታወቀው ገጠሬ ብልጥ አይደል…’’ምንም ከመንግስት ጋር ብንጣላ ሀገራችንን አንበድልም በማለት የሚጠቀሙበትን የእርሻ መሬት ግብር ሊከፍሉ መቀለ መጥተው ተቀበሉን አሉ:: ሕወሐት ደግሞ መንግስትነታችን ካላመናቹሁ ግብር ለምንድን ነው የምትከፍሉን ፤ አንቀበልም አሏቸው:: ግድ የለም ተቀበሉን አሉና እንዲህ የሚል መልእክት ላኩ…. ‘’ሃገራችኝ’’ ፤ ትክክል ትሁን ትሳሳት ፤ ታጥፋም ታልማም ፤ ሃገራችን ናት! መንግስት በሕወሐት ጭንቅላት ቢያስብ በኢህአደግ ጭንቅላት ቢያስብም ከዚህ ትንሽ የገጠር መንደር ፍክክሩን ማቋረጥ አቃተው::

ሰው ቢሳሳት ሌላ ሰው ተው የሚለው ይላካል መንግስትስ ቢሳሳት ማን ይላክለታል? እግሪሐሪባዎች ወደነሱ ሸምጋይ ይላካል እንጂ እነሱ የሚልኩት ሸምጋይ አጥተው አሁን ሲመርቁ ‘’ወደ መንግስት የሚላክ ሸምጋይ አያሳጠህ’’ ነው የሚሉት:: እና እግሪሐሪባዎች ሀገራችን የሚገባትን ገቢ ልንሰጣት ነው ተቀበሉን እያሉ ሶስት ዓመት ሙሉ ከተማ ሲመላለሱ የሚቀበሏቸው አላገኙኝ:: ማን ያውቃል ደሞ ግብር ባለመክፈል ተብለው ይከሰሱና ከዛ የባንክ ወለድም አላቹሁ ይባላል ፥ ከዛም በሰዓቱ ባለመክፈል ቅጣትም አላቹሁ ይባላል ፥ ምን የማይባሉት ነገር—-!

እግሪሐሪባ ሶስት ዓመት ሙሉ የክልልም የፈደራልም ድጋፍ ሳታገኝ ራሷን እያስተዳደረች ትገኛለች:: እቺ የገጠር መንደር ሳይታወቅ እነ ሌኒን ፥ እነ ስታሊን ፥ እነ ቲቶ ፥ እነ ማኦ ፥ እነ ካስትሮ ፥ እነ ሰንግ ፥ እነ ሆቺሚንህ የኮሚኒዝም ንድፍ ሃሳብ ማተግበር ያቃታቸውን እግሪሐሪባ ግን ተግባር ላይ አዋለችው:: እግሪሐሪባ መሬቱም የህዝብ ነው አብረን ሰርተን እንበላለን ብለው አወጁ:: ካርል ማርክስ አሁን ቢኖር ኖሮ እግሪሐሪባዎችን ይሰግድላቸው ነበር:: የማርክስ ፍልስፍናን ሌኒንና ማኦ ያበላሹትን ባለተማሩት እግሪሐሪባዎች አሁን ካሱት::

ግን እንዴት ነው ነገሩ ሶሻሊዝምን ዘለህ በአንዴ ኮሚኒዝም መሆን ይቻላል እንዴ? አብርሃ ደስታ የዚች ‘የስርዓት ዝላ’ ትንተና እንድትሰጠኝ እፈልጋለሁ:: የሆነ ሆኖ ግን እግሪሐሪባዎች ኮሚኒስት ሆነው እርፍ አሉ:: ወደ ከተማ ግቡ አንገባም ግቡ አንገባም ክርክሩ በጣም አድካሚ ሆነና አንድ የክልል ም/ፕሬዚዳንት ነው መሰለኝ እግሪሐሪባዎችን በቀላሉ ሊያሳምናቸው ነው ተብሎ ጠቅላላ ህዝቡ ወደ መቀለ ውስጥ ከሚገኙ የህዝብ አዳራሽ ለስሰባ ይጠራቸዋል:: እግሪሐሪባዎች በጣም ተደሰቱ የክልል ሁለተኛ መሪ አክብሮ ሊያነጋግረን ነው እዝግየር ያክብረው ብለው ወደ አዳራሹ ከተቱ:: ስብሰባው ስለ ከተማ መግባትና ነበር:: ሐላፊው ግን ስለ ሕወሐት ታሪካዊ አመሰራረትና አመጣጥ ፥ በትግሉ ግዜ እግሪሐሪባ የነበራት ሚና ፥ የእግሪሐሪባ ነባር ታጋዮች በማንሳት ሆዳቸውን ሊበላ ሰውዬው ተረከ…ህዝቡ የአገሩን እንዲሁም የልጆቹን ጀግንነት እየተነገረ ስለሆነ የማይካድ ታሪክ ስለሆነ ዝም ብለው አዳመጡት:: ህዝቡ ለዲሞክራሲ ታግሎ ዲሞክራሲ ያመጣ ህዝብ እንዴት ዲሞክራሲያዊ ጥያቄውን አንቀበልህም አላቹትሳ ብሎ አጉረመረመ::

ም/ፕሬዚዳንቱ ንግግሩን ቀጠለ ‘’አሁን ወደ ከተማ ትገባላቹሁ’’ አላቸው! እኛኮ ልንገባም ላንገባም መጀመርያ ማስተር ፕላኑን አሳዩን—ፕላኑ እኛን የሚያካትት ከሆነ እንገባለን ካልሆነ ግን አንገባም አሉ:: ም/ፕሬዚዳንቱ ፕላኑ ምን ይሰራላቹኋል አላቸው? ህዝቡ ፕላኑ ለምንድን ነው የማታሳዩን እናንተ አይደላቹሁም እንዴ ያወጣቹሁት? ብለው ጠየቁ:: ም/ፕሬዚዳንቱ ፕላኑ ወላ ሕወሐት ያውጣው ወላ ሰይጣን ያውጣው ወደ ከተማ ትገባላቹሁ ትገባላቹሁ አላቸው:: ሰይጣን ካወጣውማ አንቀበልም እኛኮ ‘’ሰይጣንን ወግድ ያለች ማርያም መግደላዊት የምናምን እግርጌዋ ቤቶቻችን ሰርተን የምንኖር የሰይጣን ጠላት ነን አሉት ም/ፕሬዚዳንቱን::

ም/ፕሬዚዳንቱ እንዴ እነዚህ እግሪሐሪባዎች እንደዚህ እሳት የላሱ ናቸው እንዴ አለ በሆዱ:: ንግግሩን ቀጠለ ‘’ትገባላቹሁ ትገባላቹሁ አታንገራግሩ’’ አላቸው :: ህዝቡ ትንሽ እርስ በርስ ተያየና…እንግድያውስ ያለፍላጎታችን በጠብ መንጃቹሁ ተማምናቹሁ በግድ የምታስገቡን ከሆነ ‘ዓረና’ እንሆናለን አሉት ም/ፕሬዚዳንቱን ዓይኑ እያዬ ፥ ጆሮው እየሰማና እጆቹ የሚናገሩትን እየፃፈ እያለ:: የሚገርመው ህዝቡ ‘ዓረናን እንመርጣለን’ አይደለም ያሉት ም/ፕሬዚዳንቱን ‘ዓረና እንሆናለን’ ነው! ይሄ አሁን ምን ይባላል አንድ ስርዓት በራሱ ድክመት ህዝብ ተቶት ወደ ተቃዋሚ ድርጅት መሄድ:: ም/ፕሬዚዳንቱ እየተናገራ ሳለ ህዝቡ ዓረና ሁነናል ፥ ዓረና ሁነናል እያለ አዳራሹን ጥሎ ወጣ:: ይገርማል የክልል ም/ፕሬዚዳንት ሆነህ ህዝብ ጥሎህ ወጥቶ ብቻህን ጠረጼዛ ይዘህ ትቀራለህ ፤ ቱ!

ም/ፕሬዚዳንቱ አዳራሹ መስኮት ላይ እንደ እንሽላሊት ተለጥፈው የነበሩትን የሕወሐት ፖለቲካ ሰራተኞች/ካድሬዎች/ ሰበሰበና ‘’እንደዚህ ነው እንዴ የናቋቹሁ? ጓዶች ብታምኑም ባታምኑም ተዋርደናል በቁም ሙተናል ዓይነት ንግግር አላቸው—- ቀጥሎም አሁን የምሰጣቹሁን እርምጃ ትወስዳላቹሁ አትወስዱም? አላቸው:: መቼም የፖለቶካ ሰራተኛ መሆን ለስጋህ እንጂ ለአእምሮህ እትኖርም በአንድ ድምፅ….’’ማንኛውም እርምጃ እንወሰድባቸዋለን’’ አሉና በእግሪሐሪባዎች የተናደደው የክልል አንድ ም/ፕሬዚዳንት በካድሬዎቹ መልስ በመደሰት አምቆ ይዞት የነበረውን አየር እፉፉፉ አድርጎ አወጣው!

የገጠር መንደራ እግሪሐሪባ መንግስትን ከምሯ የተጣላችው መሆኗ ሕወሐት ካወቀች በኋላ ቁጥራቸው በዛ ያሉ ፖሊሶች ወደ መንደሯ በመላክ በእያንዳንዱ አባወራ ቤት በር ላይ በመቆም ነዋሪዎቹን ወላ አላስወጣ ወላ አላስገባ አሏቸው:: ለነገሩ ፖሊሶቹ የክልል ስለነበሩ ብዙ አልፈሩም ነበር ምክነያቱም እንደባለፈው…’’አንተ የእኬሌ ልጅ አንተም ሰው ሁነህ እኛል ልትጠብቅ እያሉ ስለሚያንቋሽሻቸው አይደፍሯቸውም’’! ሌላ ስድብ ደግሞ ‘’አንተ አባትህ በደርግ ግዜ ያደረገን እንዳይበቃ አንተም መጣህ ፤ ምነው ሁሌም የሰው አገልጋይ ሆናቹሁ ልትቀሩ ማትረቡ ይላቸዋል:: ፖሊሶቹ ልክ ደቡብ ሱዳን ላይ እንደሚታዩ ታጣቂዎች የጠብመንጃቸውን አፈሙዝ ወደ ህዝብ እያደረጉ መንጎራደድ ጀመሩ:: ህፃናቶቹ ደግሞ ተሰብስበው ዘፈን ጀመሩ…. እምቢ ጫጫታ ከተማ ለምኔ ውጣልኝ ሕወሐት ዓረና አለ ለኔ ፖሊሶቹ በህፃናቱን ዘፈን በጣም ተገርመው ሳቅ በሳቅ ሆኑ!

ጠብመንጃ ይዘህ ይሳቃል እንዴ ጠብመንጃ ይዘህማ ኮስተር ብለህ ጎርደድ ማለት ነው እያሉ ሀፃናቱ የባሰ ፖሊሶቹን እስከ ሚያነቡ አሳቋቸው! ከፖሊሶቹ ጋር የፖለቲካ ሰራተኞች ስለነበሩ ህፃናቱን ማን ነው ይሄ ሁላ ዘፈን ያስተማራቹሁ ብለው ይጠይቋቸውና ልጆቹም…ማንም አላስተማረንም ራሳችን ነን ዘፈኑን ያወጣነው ይሏቸዋል::

ካድሬዎቹ በህፃናቱ መልስ በጣም ተገረሙና የሰሙትን እንደ ወረደ ወስደው ለሐላፊዎቿቸው ተነተኑላቸው:: ሕወሐት ይሄን ሁላ ውርዴትና ጉዷን ከሰማች በኋላ ሳምንት ሙሉ ሃዘን በሃዘን ሆነች:: ያው ሕወሐት ሐዘን ሲያጋጥማት ስብሰባ ነው የምታበዛው ፤ ስትሰበስብ ሰነበተች:: እንደሰማሁት ከሆነ ከግማሽ በላይ የእግሪሐሪባ ህዝብ ወደ ዓረና ገብቶ የአባልነት ካርድ ተሰጥቶታል:: የህወሐት ፍራቻ ደግሞ የእግሪሐሪባ ዓረና መሆን ወደ ሌሎች የገጠር መንደሮች ይስፋፈል ፤ ገና 23 ዓመት ብቻ ያደረገው ስልጣን እንዳይሸረሸር ሰግታ ነው:: ሕወሓት መላ ዘየደችና እነዚህ የእግሪሐሪባ አስተባባሪዎች ህዝቡን ወደ ዓረና ቀይረዋል ያለቻቸውን ሰዎች ተንኮል ስትጠነስስ ሰንብታ ክሱ በማየታወቅ መንገድ ሁለት ቁልፍ ሰዎች በቁጥጥር ስር አዋለች:: ያው እኔም ስራዬ ከዚህ ጋር የተያያዘ ስለሆነ ‘’ለምን ይታሰራሉ ብለው ሲያወሩ የነበሩትን የስራ ባልደረቦቼ ባገኘሁት መረጃ መሰረት ስለ ጉዳዩን ሳጣራ….ይገርማል…. የተከሰሱበት ጉዳይ በግልባጭ ወደ አለቃዬ ተልኮለታል…ክሱን ሳነበው—-እከሌ እከሌ እንዲሁም እከሌ እከሌ የተባሉ ‘የህፃናትን መብት በመርገጥ የህፃናት መብት አስከባሪ የተባለ ነዋሪነቱ ኒውዮርክ የሆነ ድርጅት ክስ አቅረቦላቸዋል’:: ህፃናቱ የትምህርት ዕድል መንግስት አመቻችቶላቸው ሳለ እንዳትማሩ በማለት ፤ የህክምናና የምግብ አቅርቦት ከውጭ አገር በውድ ተገዝቶ የመጣ ምርት እንዳይታከሙ እንዳይመገቡ አደረጉ:: ህፃናቱ ነገ እቺን አገር በእውቅት እንዳያገለግሏት ፥ የተሟላ ተክለ ሰውነትና ጤናማ አእምሮ እንዳይኖራቸው ተደርገዋል ይላል ክሱ::

ሕወሐት ለዚች ሚጢጢ የገጠር መንደር ያን ያህል መከራ ማውረድና ወደ ከተማ በማስገባት ምንድን ነው የምትጠቀመው? ህዝበ ራሱ መርጦ ወክዬሃለሁ አስተዳድሩኝ ብሎ ስልጣን መስጠቱን ረስተው ያሰቃዩታል ፤ ለነገሩ ወላጆቻቸውን የሚደበድቡ ልጆችም አሉ እየተባለ አይደል እኔ እንኳ እስካሁን አላየሁም ከሕወሐት ውጭ:: ሕወሐቶች እንዲህ እግሪሐሪባን አጥብቀው ወደ ከተማ መግባት የፈለጉበት ምክንያት ‘’ምናልባት ጠንቋይ ጋር ሄደው እግሪሐሪባ ከተማ ካልገባች ስልጣናቹሁ ያበቃል’’ ብሎ ነግሯቸው ይሆናል:: ወይ ጠንቋይ ፤ በግልም ወደ ጠንቋይ ፥ በማሕበርም ወደ ጠንቋይ ፥ በድርጅትም ወደ ጠይቋይ……ለማንኛውም ሜ/ጀነራል ሐየሎም አርአያ በአንድ ወቅተ የተናገራትን ትጠቅመን ይሆናል……. ………ወደ ህዝብ የተኮሰ ውድቀቱን አፋጠነ……..!

Advertisements

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out / Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out / Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out / Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out / Change )

Connecting to %s