ግልጽ ደብዳቤ ለአቶ ግርማ ብሩ – (እዶሳ አ ቱፋ)

አቶ ግርማ ብሩ በዩናይትድ ስቴትስ የኢትዮጵያ መንግስት አምባሳደር።  በቅድሚያ ባህላዊዉና ወገናዊዉ ሰላምታዬ ይድረስዎት። በማስከተል ይህን ግልጽ  ደብዳቤ እንድጽፍሎት ያነሳሳኝ አልያም ያስገደደኝ በቅርቡ የድርጅቶትን የኢህ አዴግን ድል  ሀያ ሶስተኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ አትላንታ ከሚገኘዉ ጽናት ሬድዮ ጋይ ያደረጉት ቃለ መጠይቅ መሆኑን ልገልጽሎት እሻለሁ።http://www.ethiotube.net/video/31036/Tsenat-Radio-Atlanta–Solomon-Tekalign-interviews-Ambassador-Girma-Biru–May-2014

ከቃለ መጠይቁ በእኔ አረዳድ እጅግ አስተዛዛቢ፣ አሳሳቢና አነጋጋሪ ጉዳዮችን  አድምጫለሁ። በእርግጥ ከኢሃዴጋዉያን አንደበት የተሻለ አልያም የተለዬ ጉዳይ መጠበቅ  ድርጅቱን አለማወቅ ነዉ። በመስማቴ የታዘብኳቸዉንና ያዘንኩባቸዉን ነጥቦች ከማንሳቴ አስቀድሜ እንደ አንድ የኦሮሞ ብሄር ተወላጅ ስለ እርሶና ስለ ድርጅትዎ በተለይ ኦህዴድ ያለኝን እይታና ግንዛቤ ባጭሩ ላነሳልዎት እሻለሁ።

በመጀመርያ ድርጅትዎ ኦህዴድ እርስዎና ባልደረብዎችዎ ፕሮግራሙን ሳትጽፉለት  ወይም ለመጻፍ ሳትታደሉ ሌሎች ወገኖች በሚመቻቸዉ ባሰቡትና በቀየሱት ተመስርቶ  በዚሁ ቅኝት ግዞት ተይዞ ወክለዋልሁ የሚለዉን የኦሮሞን ህዝብ የልብ ትርታ ለመስማት ሳይታደል እነሆ ሀያ አራት ኣመት መቁጠሩን እናንቴም ህዝቡም በወል እንረዳዋለን።

ተመስርቶ በዓመቱ ለስልጣን የታደለዉ ይህ ድርጅት በበርካታ ወሳኝና ፈታኝ  በሆኑ ጉዳዮች ላይ እወክለዋለሁ ከሚለዉ ህዝብ ጎን አለመሆኑን እንድያዉም በተቃርኖ  የሚቆም መሆኑን በተግባር ያሳዬ ከሱ ሌላ እምነቶችም አቋሞችም ደካማና ጸረ ህዝብ  መሆናቸዉን ሊያሳምነን ስማስን የኖሬ ድርጅት ነዉ። ቆመለታለሁ የሚለዉ ህዝብ  እንዳዘነበትና ከልቡ እንዳራቀዉ ቆሞልናል የሚሉት ፈጣሪዎቹ ደግሞ ዉስጡን ለቄስ  ብሉም ላይ ላዩን ሲያወድሱትና ሲያሞግሱት ኖረናል።

ይህን ስል ድርጅትዎን ስለማልደግፍ አልያም ሲለሚቃወም በጥላቻ መንፈስ ተነሳስቼ ሳይሆን እኔም እንደብዙዎች በቅርብ ርቀት ስልማዉቀዉ ያለዉም እዉነታ በጋሃድ የሚታይ በመሆኑ ከዚሁ በመነሳት ነዉ። ከአንደበታችሁ የሚንሰማቸዉ፣ ከተግባሮቻችሁ የሚናያቸዉ አልፎ ተርፎም ዘመን አልፎ ዘመን ስተካ የሚፈራረቁብን ግፍና መከራዎች ገሃድ ማስረጃዎች በመሆናቸዉ ነዉ።

ምንም እንኳን የድርጅታችሁ ዓላማዉም አቅጣጫዉም ከኦሮሞ ህዝብ ዘላቂ ጥቅም አንጻር በርካታ አሳሳቢ ጉዳዮች ብኖሩትም ከፍሎቻችን በቅንነት ከሚናስባቸዉ እዉነታዎች ዉስጥ ጥቂቱ በዚህ ድርጅት ዉስጥ አንድ ቀን የህዝባቸዉ ጥልቅ ብሶት ተሰምቷቸዉ ድምጻቸዉን ከፍ አድርገዉ የሚያሰሙ፤ ገሃዱን እዉነታ በአደባባይ ወጥተዉ የሚመሰክሩ ግለሰቦች አይጠፉም የሚለዉ እሳቤ ነዉ። ይህን ስል ከእንግድህ በቃን አትፈለጉም ተብለዉ ከተጣሉ በሃላ የሚናገሩትን ሳይሆን ገና ወንበራቸዉ ላይ እያሉ ለእዉነት ስሉ ጥቅማቸዉንም የሚሰዉትን ለማለት ነዉ። በየዋህነት የዚህ አይነት እሳቤ ከሚያስቡት መካከል እኔም አንዱ ነኝ። በዚያ ደረጃ ከሚጠብቃቸዉም የኦህዴድ ከፍተኛ አመራሮች አንዱ እርስዎ ይሆናሉ ብዬም ባስብ የተወሰኑ መነሻዎች ስላሉኝ ነበር። እዉቀትዎም ሆነ የበርካታ ዓመታት ተሞክሮዎችዎ ለዚህ ያበቃዎታል ብዬም ነበር ይህን አስተሰሰብ ተሸክሜ የኖርኩት።

በወገንዎ በኦሮሞ ህዝብ ላይ የተነጣጠረዉ መሰረተ ሰፊ የጥቃት ዘመቻ ቅርጹንና ይዘቱን ይቀያይር እንጂ እያደር ከማገርሸት ሊመለስ አልቻለም። እኛም ወገንዎችዎ ብሶታችንን ስናሰማና ለመፍትሄም ስንጮህ እንደናንቴ አገላለጽ በሌላዉ ህዝብ ላይ ጥላቻ አድሮብን፣ ለራስ ብቻ ከማሰብ በአጭሩ በጠባብነት ሳይሆን ግፍና መከራዉ ስለበዛብን ሰሚ እናገኝ ይሆን ከምል መነሻ ነዉ። ታድያ አለመታደል ሆነና ፍትህ ጠማኝ ብሎ የሚጮሄዉ ሁሉ ጥይት እየጎረሰ ዳግም እንኳን ልጮህ ላይተነፍስ ጥሙን ሳይሆን እስትንፋሱን መቁረጥ ሆነ መልሳችሁ።

ለዚህ ጽሁፍ ወደ አነሳሳኝ የሬድዮ ቃለ መጥይቅ በመመለስ ትዝብቶቼን ላቅርብሎት፥ ያልገቡኝንም ልጠይቆት።

አንደኛ : ስለ ህገ መንግትዎ ዲሞክራሲያዊነት ሲያወድሱ « ህገ መንግስታዊ ስርዓቱ የልዩነት ሃሳብን በነፃነት ማቅረብን ይፈቅዳል። የሁከት ጎዳናን የመረጡት ወገኖች በነፃ ምርጫ የሚያሸንፉ መስሎ ያልታያቸዉ የህዝብን ዳኝነት ለመቀበል ዝግጁ ያልሆኑ፤ ከሰለጠነዉ የዲሞክራሲ አሰራር ሃይልን አማራጭ አድርገዉ የሚወስዱ ናቸዉ » ስሉ እጅግ አስተዛዛቢና በእርሶ ደረጃ ካለ ሰዉ የማንጠብቀዉን ቃል ተናገሩ።

ለምን ብሉ – እርግጥ ነዎት ህገ መንግስቱ ሃሳብን በነፃነት መግለፅን ይፈቅዳል። ነፃ ዉድድርንም ይፈቅዳል። በዚህ ረገድ እንከን የለዉም። ዳሩ ግን ህገ መንግስቱ ለራሱስ መች ነፃነት አገኘና ? ሃገሪቱ እየተመራች ሳይሆን እየተገዛች ያለችዉ በህገ መንግስቱ  ሳይሆን በድርጅታችሁ መመርያ ስለመሆኑ ምን የሚያከራክር ነጥብ አለዉ?

« በምርጫ ዉድድር ለማሸነፍ እምነት ያጡ ወገኖች » ስሉስ ይህ ወቀሳ  ኢህአዴግን ነዉ ወይስ ለሎችን የሚገልፅ ይመስሎታል ? ከቶም በነፃ ዉድድር ማሸነፍ እንደማይችል በተግባር ያረጋገጠዉና የሃይል ጎዳናን የመረጠዉ ኢህአዴግ ስለ መሆኑ ከምርጫ ዘጠና ሰባት ኣላስተዋሉምን ? የኢትዮጲያ ህዝብ እኮ ድርጅታችሁን እንደማይሻ አስረግጦ ተናግሯል።

« ተቃዋሚ ሃይሎች ከሰለጠነዉ መንገድ የሃይል ጎዳናን ይመርጣሉ » ስሉ ላለመሰልጠናችን መንስኤዉ ድርጅታችሁና እናንተዉ አመራሮቹ ስለመሆናችሁ ምን ጥያቄ አለዉ? ህዝቡን እኮ « ከዜላለም ባርነት የአንድ ቀን ነፃኔት » ብሎ ሞትን እንድጋፈጥ እያስገደዳችሁት ነዉ።

የኦሮሞ ህዝብ ለፍትህ እንጂ ለስልጣን ስል እየሞቴ እንዳልሆነ ልቦናዎ አያጣዉም። ምክንያቱም ለአንድ የኦሮሞ ብሄር ተወላጅ ስልጣን ለማግኘት እጅግ ቀላሉና ርካሹ መንገድ የኦህዴድ አባል መሆን እንደሆነ እናንተም ህዝቡም ጠንቅቀን ስለምናዉቀዉ ነዉ። ታድያ ፍትህንና እዉነትን ፍለጋ ካልሆነ ዉጣ ዉረድ የበዛበትን መንዋእትነት ጠያቂ የሆነዉን ሌላ መንገድ መምረጥ ለምን አስፈለገ?

ስለ ስልጣን ካነሳን አይቀር አንድ ነገር ልበልዎት። ኦህዴድ ሀያ ሶስት ዓመት በስልጣን ላይ የቆየዉ ህዝብ ወዶትና መርጦት አይደለም። ህዝብ የሚወደዉ ድርጅት ብሆን በርካታ አዳዲስ ፍሬዎችን በማፍራት አሮጌዉን በአዲስ ያረጀዉን በወጣት እዬተካ በተለሳለሰና ጠናማ በሆነ መልኩ ይጓዝ ነበር። ታድያ ድርጅታችሁ ለዚህ እዉነታ ባለመታደሉ አይደል እናንተዉ በጣት የሚትቆጠሩ አመራሮች ለዚህ ሁሉ ዜመን ከአንድ ወደ ሌላ ወንበር እየተሸጋገራችሁ ቀዳዳዉን ሁሉ ለመድፈን እዬማሰናችሁ በህዝቡ የብሶት ወላፈንም እየተፈጃችሁ ያላችሁት? ስለዚህ የስልጣን ጥሙ ከማን ዘንድ እንዳሌ ያዉቁታልና በሌላዉ ማላከኩ ይቁም እላለሁ።

እባክ ዎትን እስኪ አሁንም አንድ እድል ነፃ የምርቻ መድረክ ይፍቀዱና የኢትዮጵያ ህዝብ ዳኝነቱን ይስጥ።

ሁለተኛ : የኦሮሞ ተማሪዎች ያነሱትን ህዝባዊ የመብት ጥያቄ አስመልክተዉ በተናገሩት ላይ የሚከተሉትን አስተዛዛቢ ነጥቦች አንስተዋል። በሀገሪቱ ከሃያ ሚሊዮን በላይ ተማሪዎችን ወደ ት/ቤት መሄድ እንዳስቻላችሁ ከዚህም ዉስጥ ግማሽ ሚሊዮኑ ወደ ዩኒቨርስቲዎች እየሄዱ መሆናቸዉን በዉዳሴ ከገለፁ በሃላ « ተማሪዎቹ ለተቃዉሞ የተነሳሱት በተቃዋሚ ድርጅቶች ተቀስቅሰዉ ነዉ » ስሉ ተማሪዎቹ በራሳቸዉ አዉቀዉም ሆነ ተነሳሽነት ኖሮአቸዉ ይህን ጥያቄ እንደማያነሱ ቁጥራቸዉ በዛ እንጂ ለዚህ የሚሆን ብቃት የላቸዉም የምል እንደምታ ባለዉ መልኩ ገለፁአቸዉ። የኦሮሞ ተማሪዎች በወገኖቻቸዉ ላይ እየደረሰ ያለዉን ግፍና መከራ አይረዱም፤ ብረዱ በራሳቸዉ ተነሳሽነት ለመጠየቅ ብቁ አይደሉም ብለዉ ያስባሉን ? ይህ ከሆን የት/ፖሊሲዎትን ይመርምሩ። የነገዉ ሃገር ተረካቢ ዜጋም በምን ደረጃ ላይ እንዳሌ ያጢኑት።

ከዚህም አያይዘዉ « ተቃዋሚ ሃይሎች በሸረቡት ሴራ ወጣቱን/ ተማሪዉን የእሳት እራት አድርገዉታል » ስሉ እጅግ አሳዛኝ አስፈሪና ኣሳሳቢ ነጥብ አንስተዋል። ተማሪዉ በራሱም ይሁን በለሎች ተታሎ ይህን ጥያቄ ይዞ ተነስቶ ከሆነ መልሳችሁ እሳት መሆኑ ነዉ ? የሃገሪቱ ዘጎችስ ተቃዉሞአቸዉን ለማሰማት ልዩነታቸዉን ለመግለፅ ብሻቸዉ እሳቱን እንደት ይቀርቡታል ? ከእሳቱ ለመታደግስ ከዘግነት በተጨማሪ ምን ዋስትና ማግኘት ያስፈልግ ይሆን ? መልሱን ለእርሶና ለድርጅትዎ።

ሶስተኛ : በደረሰዉ የህይወት መጥፋት መንግስትዎ እንደሚያዝን የገለፁበት ጉዳይ ነዉ። መንግስትዎ ስለ ማዘኑ እርግጠኛ ነዎት? መንግስት ስለማዘኑ እስካሁን ለምን ይፋ አልተደረገም? በቀጣይ ላለመገደሉስ ምን ዋስትና አለዉ ዜጋዉ? ከዚህ ቀደም በኦሮሚያ፣ በሲዳማ፣ በጋምቤላ፣ በሶማሌ፣ በአፋር ወዘተ ለተፈፀሙት የጅምላ ግድያዎች መንግስትዎ በየትኛዉ ተፀፅቷል ? ለመሆኑ የትኛዉንስ በገለልተኛ ወገን እንድጣራ ፈቅዷል ? ዳሩ ግን ካለፉት ሁለት ዓመታት ወድህ እያዬነዉና እየተማርን ያለነዉ ህዝብ ሞትን በመፍራት መብቱን ከመጠየቅ እንደማይቆጥብና ይህንንም በተግባር እያሳዬ መሆኑን ነዉ። ህዝቡም ለመብቱ ፅኑ መሆኑን ገዢዉ አካልም እሳቱን ከማቀጣጠል ሌላ አማራጭ እያጣ መምጣቱን ነዉ እዉነታዉ እያሳየን ያለዉ።

 አራተኛ : ያረቀቃችሁት የአዲሱ ማስተር ፕላን ጉዳይ ነዉ። « ተማሪዎቹ በቂ እዉቀትና ግንዛቤ ሳይኖራቸዉ ድብቅ ዓላማ ባላቸዉ ወገኖች ተታለዉ ነዉ ጥያቄ ይዘዉ የተነሱት። ፕላኑ ገና በረቂቅ ደረጃ ነዉ ያለዉ። ገና ለህዝብ ቀርቦ ዉይይት ይደረግበታል። ስልዚህ የሚያሰጋና ለቅሬታ የሚያደርስ ነገር ኣልነበረበትም »። ስሉ የተማሪዉን ጥያቄና የህዝቡን ቅሬታ አጣጥለዉታ።

 አዲሱን ማስተር ፕላን የኦሮሞ ህዝብ በሩቁ ብፈራው እዉኔት አለዉ። ምክንያቱም በየትኛዉም ጉዳይ ላይ ህዝብን ማማከር፤ የዝብን ስሜት ማዳመጥ የሚባል ነገር በልምዳችሁ ዉስጥ ስልማይታወቅ ዛሬ ምን አዲስ ነገር ይፈጠራል ብሎ ነዉ ህዝቡ ያወያዩናል ብሎ የሚጠብቃችሁ? ከናንቴ ለላ አቋም ያላቸዉን ድርጅቶች በሽብርተኝነት እዬፈረጃችሁ ከሃገር ስታሳድዱ፤ የመረዳጃ ተቋሞቻችንን በአዋጅ እያፈረሳችሁ ንብረታቸዉን ስትወርሱ፤ ህዝቡን በገፍ እንድ ናዚዉ ስርዓት ወዴ እስር ስታግዙት፤ የፍንፊኔ /አዲስ አበባ/ን ክልል በመቶ ሺህ የሚቆጠር አርሶ አደር ከቤት ንብረቱ አፈናቅላችሁ በድህነት ተጎሳቁሎ ተከብሮ በኖረበት መንደሩ በበረንዳ ወድቆ በረሃብ እንድሞት ስትፈርዱበት፤ ከቀየዉ ላለመፈናቀል የሚያሰማዉ ጩሄት ሰሚ እንዳያገኝ በቀላጤ አዋጃችሁ የፍርድ ከለላ ስትነሱት፤ ፊንፊኔ የኦሮሚያ እምብርትነቷን ነፍጋችሁ መስተዳድሩን በህዝቡ ጩሄትና ደም ላይ እየተረማመዳችሁ አዉጥታችሁ ወደ ሌላ ስትሰዱበት፤ ስለ ህዝቡ የሚቆረቆሩትንና የሚናገሩትን በፈጠራ ወንጀል በየማጎርያችሁ ስታሰቃዩአቸዉ ህዝቡ በምን ያምናችሃል?

ሃያኛ ዓመት ልደቱን ሊያከብር በደረሰዉ ህገ መንግስት አንቀፅ 49-5 የኦሮሚያ ክልል በፊንፍኔ ላይ የሚኖረዉ ልዩ ጥቅም ይጠበቅለታል ይላል። የዚህን አንቀፅ አፈፃፀም አዋጅ ላለማዉጣት ታቅባችሁ የኦሮሞን ህዝብ ጥቅም በግልፅ ወደ ጎን በመተዉ ዛሬ ለግዛት ማስፋፋት ልዩ ራእይ ሰንቃችሁ መነሳታችሁ በራሱ የትልቅ አደጋ ምልክት ነዉ።

ለነገሩ ከከተማዉ ዉጪ ባሉት አዋሳኝ ወረዳዎች የሚገኙ በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ አርሶ አደሮች በተመሳሳይ ሁኔታ ከማሳቸዉ እዬተፈናቀሉ እንደሆነ የቀሩትም በቁጥጥር አልባዉ የልማት ተልእኮ ወንዞቻቸዉና ኩሬዎቻቸዉ በመርዛማ ንጥሬ ነገሮች እዬተመረዙ እንስሶቻቸዉ በገፍ እያለቁባቸዉ እንደሆነ እርሶም ጠንቅቀዉ ያዉቁታል። ህዝቦቹም እጅግ በከፋ የተስፋ መቁረጥና የከለላ ማጣት አደጋ ላይ እንዳሉ እንኳን ለእርሶና ለእኛ ለወገኖቻቸዉ ሌላዉ ዓለም የአደጋዉን አሳሳቢነት ተገንዝቦ እየጮሄላቸዉ ነዉ ያለዉ።

ከተሞቹ አይደጉ፤ አካባቢዉ አይልማ ብሎ የተቃወመ አልያም በከንቱ የጮሄ የለም። እድገቱም፣ ልማቱም የኦሮሞን ህዝብ እዬበላና እያጠፋ አይሁን ነዉ። በፊንፍኔ የተፈፀመዉ ግፍ በሌላዉም አይደገም ነዉ። ይህ ተግባር የዘር ማጥፋት ወንጀል ስለሆነ ይቁም ነዉ። በዚህ መርሃግብር መሰረት የኦሮሞ ህዝብ መፈናቀሉና ለእልቂትም መዳረጉ ብቻ ሳይሆን ታሪካዊ እሴቱ ጭምር ነዉ እንድጠፋ እየተደረገ ያለዉ። ይህ ደግሞ ዓላማዉ ግልፅ ያልሆነ ለህልዉናችን የሚያሰጋን አደጋ ነዉ። በዚህ ተግባር ዉስጥ ድርጅትዎ ምናልባት ለመወሰን ባይታደልም ለማስፈፀሙ ግን ግንባር ቀደም ነዉና የአደጋዉን ክፋት ተገንዝቦ፤ የህዝቡን የልብ ትርታ ሰምቶ አካሄዱን ያርም ነዉ። ከቻለም የከዚህ ቀደም ተግባራቱን መለስ ብሎ ይመርምር ነዉ።

አንድ ህዝብ ከተፈጥሮአዊ አካባቢዉ እየተፈናቀለ በሄደ ቁጥር ቋንቋዉ፣ ባህሉ፤ ቁሳዊ እሴቶቹ ወዜተ ከመጥፋታቸዉ ባሻገር ሰብዓዊ ክብሩን ሳይቀር እየተገፈፈ ይሄዳል። ይህ ደግሞ ምንም ፍልስፍናም አይደለም። በወል በተግባር እያየነዉ ያለነዉ ጉዳይ ነዉና።

አምስተኛ : በንግግርዎ መግቢያ ላይ ኦሮሚያ ዉስጥ ተቃዉሞ በተቀሰቀሰበት ወቅት በቦታዉ ስላልነበሩ ዕዉነታዉን በትክክል መግለፅም ሆነ ዳኝነት መስጠት እንደሚከብድዎት በመናገር ዕዉነታነት ያለዉ አቀራረብ ቀረቡ። ከደቂቃዎች ንግግር ብሃላ ግን « የፀትታ ሃይላችን በከፍተኛ ደረጃ ከታጠቀ ሃይል ጋር ነዉ የተጋፈጠዉ » ስሉ ባልነበሩበትና ባላዩት ጉዳይ ምስክርነትዎን ከመስተትዎ በተጨማሪ « እንዲያዉም የሰዉ ህይወት የጠፋዉ በወድያ በኩል በተተኮሰ ጥይት ነዉ » ስሉ ፍርደ ገምድል የሆነ ዳኝነት ሰጡ። ይህ አገላለፅ በሃገሪቱ የዳኝነት ስርዓት በምን ደረጃ ላይ እንዳለ የሚያሳይ ግልፅ ማስረጃ ነዉ። እርሶ አሜሪካ ተቀምጠዉ መበየን ከቻሉ ሃገር ቤት ያሉት ባለስልጣናት ደግሞ አይተናል ሰምተናል እያሉ ምን ይሉ ይሆን?

እዚህም ላይ አንድ ትዝብቴን ላነሳሎት እሻለሁ። የአብዛኛዉ ህዝብ እንደሚሆንም ገምታለሁ። የአምቦ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች እንደሌሎች ሁሉ በማስተር ፕላኑ ላይ ያላቸዉን ቅሬታ በመግለፅ ያላቸዉን ጥያቄዎች መንግስታዊ ምላሽ እንድያገኙ ለሚመለከተዉ አካል አቅርበዉ በተመለሱ በማግስቱ ፍፁም ባልተጠበቀ ሁኔታ በከተማዉ ዉስጥ ለተቀሰቀሰዉ ሁከት የመንግስት እጅ ስለ መኖሩ የሚያጠራጥር  አይደለም። ምክንያቱም የተፈፀመዉ የዘረፋና የንብረት ማዉደም ተግባር ከቶም ከተማሪዎቹ ጥያቄም ሆነ ከተቃዉሞአቸዉ ጋር ጉድኝት የለለዉ ሆን ተብሎ የተወሰነ የህብረተሰብ ክፍልን ለመወንጀል የተቀነባበረ፤ በማግስቱም የተለመደዉ ኢህአዴጋዊዉ የተለቪዥን ድራማ የተሰራለት፤ አምቦን በመምታት ሌላዉን ማስተኛት የሚል ይዞታ  የታዬበት በመሆኑ ነዉ። ይህ ደግሞ ምንም አዲስ ክስተት አይደለም። ህዝቡ  የለመደዉና ምናልባትም ከእያንዳንዱ ክስተት ጀርባ የሚጠብቀዉ ነዉ። ህዝቡ ካካበተዉ  ተመክሮ አንድ ክስተት ስፈፀም ሁለተኛዉን በእርግጠኝነት የመናገር ሶስተኛዉን ደግሞ መገመት በሚችልበት ደረጃ ነዉ ያለዉ።

ለመሆኑ ሰላምና መረጋጋት ሰፍኖበታል በተባለለት ሀገር በከፍተኛ ደረጃ የታጠቄ ሃይል አምቦ ድረስ ከዬት መጣ? የዚህ መሰል ችግር ካሌ ምን ያክል ህዝቡ ከመንግስት ጎን መሆኑን መመርመር ያሻል።

በመጨረሻም ከአንድ መንግስት ሀላፊነቶች አንዱ ፍትሃዊ የሃብት ክፍፍል በዜጎች መካከል እንድኖር ማስቻል ነዉ ። ይህ ግን ከአንዱ ነጥቆና አደህይቶ፤ በተልይ በተፈጥሮ ከተቆራኘበት መሬቱ አፈናቅሎና ህልዉናዉን አጥፍቶ ልሆን አይገባዉም ባይ ነኝ። የህዝብን ጥያቄና ብሶት መስማት ለህዝቡም ለራስም ክብር ነዉ። « ይህ የጥቂቶች ጥያቄ ነዉ ፤ የስልጣን ጥመኞች ድብቅ ሴራ ነዉ » እያሉ ዕዉነትን ማድበስበሱ ችግርን እንጂ መፍትሄን አይወልድምና።

Contact : idosaatufa@hotmail.com

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out / Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out / Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out / Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out / Change )

Connecting to %s