የሕዳሴ አብዮት አተገባበር!

(ተመስገን ደሳለኝ)

ባለፉት ሁለት ሳምንታት በተከታታይ ባቀረብኳቸው ጽሑፎች ገዥው-ግንባር የመረጠው ስሁት መንገድ፣
ኢትዮጵያችንን ለሳልሳዊው አብዮት እያዘጋጃት መሆኑን ማውሳቴ ይታወሳል፡፡ ይህ የለወጥ መስመርም “የሕዳሴ
አብዮት” የሚል ስያሜ ኖሮት፣ ሁሉን አሳታፊ ፖለቲካዊና ማሕበራዊ ንቅናቄ በመፍጠር አገሪቱን በዳግም
ውልደት ለማንፃት ብቸኛ አመራጭ የመሆኑ ጉዳይ በስነ-አመክንዮ ተሰናስሎ ቀርቦበት ነበር፡፡ በዚህ ተጠየቅ
ደግሞ አብዮቱን ከዳር ለማድረስ ሊተገበሩ የሚችሉ (በሰላማዊ ትግል ማዕቀፍ ውስጥ ያሉ) ስልቶች እና
በመጀመሪያው የንቅናቄው ምዕራፍ ሥርዓቱ ለመመለስ ሊገደድባቸው የሚገቡ ጥያቄዎችን እንዳስሳለን፡፡

ለምን እንሞታለን?

የዓለም ታሪክ አምባ-ገነኖች እብደታቸውን እንዲተገብሩ የሚያስችላቸው የታጠቀው ኃይል (ጦር ሠራዊት፣ ደህንነት እና ፖሊስ)
ስለመሆኑ አያሌ ማሳያዎችን ዘርዝሮ ያስረግጣል፡፡ የኢትዮጵያችን የቅርብ ጊዜ ታሪክንም ብንመለከት፣ የአፄ ኃይለስላሴ ጨቋኝ
አስተዳደርን ግማሽ ክፍለ ዘመን አፋፍ ድረስ ተሸክመው የተጓዙት እነዚህ ኃይሎች መሆናቸው ጉዳዩን አምነን እንድንቀበል ያስገድደናል፡፡
የኮሎኔል መንግስቱ ኃይለማርያም በላኤ-ሰብ ዘመን በታሪክነት ተመዝግቦ ለመታወስ የቻለውም ይህንኑ ክፍል አጥብቆ በመያዙ መሆኑ
የትላንት ክስተት ነው፡፡ ባለፉት ሁለት አስርታት ያስተናገድነው የኢህአዴግ ብልጣ ብልጥ አምባ-ገነን አስተዳደርም ከከፋፍለህ-ግዛ ስልቱ
በተጨማሪ ዋና መሰረቱ ጠብ-መንጃ አንጋቹ አካል ለመሆኑ ይህ ትውልድ የአይን እማኝ ነው፡፡ አዲሱ የሕዳሴ አብዮታችንም በዚህ ኃይል
ላይ ትኩረት ያደርግ ዘንድ የተገደደበት መግፍኤ ይኸው ነው፡፡

ከግፉአኑ (ከጭቁኖቹ) አብራክ የወጣው ጦር ሠራዊት ‹‹ተኩስ!?›› ተብሎ በታዘዘ ቁጥር ስለምን አምሳያው የመከራ ተቸንካሪ ላይ ሁሌ
ጥይት እንደሚያዘንብ እጅግ ግራ አጋቢ ነው፡፡ እውን የህፃናትን ግንባር የሚበረቅሰው፣ እህት-ወንድሙን አነጣጥሮ የሚጥለው ሥርዓቱን
ተቀብሎት፣ ትዕዛዙንም አምኖበት ነው ወይ? በጉልበትም ሆነ በሥነ-ምግባር ከሚልቃቸው ግለሰቦች የሚተላለፍለትን መመሪያ እየተገበረ
ሰጥ-ለጥ ብሎ የሚገዛው የግል ጥቅም አመዝኖበት? ወይስ ለአለቆቹ የዘፈቀደ ተግባር ሎሌ ሆኖ? …የደህንነት መ/ቤቱ አባላትስ እንዲህ
ታች ወርደውና አጎንብሰው የፓርቲ አገልጋይ የመሆናቸው ምስጢር ምን ይሆን? ከገዥው-ግንባር የተለየ የፖለቲካ አመለካከት ያላቸውን
ድርጅቶች ቢሮ፣ አመራሩን እና ጋዜጠኞችን በመሰለል መጠመዳቸው የ‹‹እንጀራ›› ጉዳይ ብቻ ሆኖባቸው ነውን? ንፁሀንን በጠራራ ፀሀይ
ሳይቀር አፍነው ለስቅየት አሳልፈው እንዲሰጡ የተገደዱበት መነሾስ ምንድር ነው? …የፖሊስ ሠራዊትስ የሥርዓቱ የማጥቂያ መሳሪያ
በመሆን እንዲህ ማዕረጉን አቅልሎ ለሀፍረት የተዳረገበት ጉዳይ በማን እርግማን ይሆን? …እኮ ለምንድር ነው የእነርሱንም ጭምር ነፃነትና
ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት የሚያውጅ ጥያቄ ባነሳን ቁጥር ደማችንን ደመ-ከልብ የሚያደርጉት?

እነዚህን ጥያቄዎች ለመመለስ ሰፊ ጥናት የሚጠይቅ መሆኑ ሳይዘነጋ፣ የንቃተ ህሊና ማነስ እና ነፍሰ-ገዳይን አወዳሹ ነባር ባሕላችን ከገፊ-
ምክንያቶቹ መካከል ስለመጠቀሳቸው ለመናገር ግን የምሁራን ትንተና የሚያስፈልገው አይመስለኝም፡፡ ከዚህ አኳያም ሕዳሴን መሰረት
የሚያደርገው አብዮታችን ከትኩረት ማዕከሉ ቀዳሚ አድርጎ መጠነ ሰፊ ቅስቀሳና የንቃት ሥራ በመስራት፣ ባለፉት ዘመናት የጭቆናው
አስፈፃሚ ሆኖ በታሪክ ጥቁር መዝገብ የሰፈረውን ታጣቂ ኃይል፣ ወደ ተባባሪነት (ሕዝባዊነት) መለወጥ እንደሚኖርበት ተረድቶ መፍትሔ
ካላበጀለት በታሪክ ፊት ከሥሉስ ውድቀቱ የሚታደገው አይኖርም፡፡ በአናቱም አብዮቱ ክብሩን ሊመልስለት እንጂ፣ ነቅንቆ ሊበትነው
የተነሳሳ እንዳልሆነ ታጣቂ ኃይሉን ማሳመን የእኛ ዓብይ ተግባር ነው፡፡ እነርሱ አንድም በኑሮ ውድነት፣ ሁለትም ነገን በመስጋት ስር
እንዲያድሩ ተቀይደው ነጻነታቸውና መብታቸው የተገፈፈ የመሆኑን እውነታ አስረግጦ ነግሮ ከሕዝብ ጎን በመቆም ሚናቸውን ይወጡ
ዘንድ ማግባባት አብዮታዊ ግዴታ ለመሆኑ ነጋሪ አያሻም፡፡ ከለውጡ በኋላም ሠራዊቱ ከአገር አለኝታነቱ በዘለለ፣ ከአድሎአዊነትና ከእርስ
በርስ (ከዘውጋዊ) ጥላቻ በፀዳ ፍትሓዊ አስተዳደር ተጠቃሚ የመሆኑን ጉዳይ ማሳመኑ በቀውጢው ሰዓት ወሳኝ ድጋፍ ለማግኘት ጠቃሚ
ነው፡፡ የጥቂት ጀነራሎች የሙስና ወንጀልም፣ አቻ ባልደረቦቻቸውንም ሆነ መላ ሠራዊቱን የሚወክል አለመሆኑን ከዘለፋ በራቁ ጨዋ
ቃላት መወትወት ጉልህ አስተዋፅኦ አለው፡፡ ይህን ታላቅ ተልዕኮ ለማሳካት በተለይም የአዛዦቹም ሆነ የተራው ወታደር ቤተሰብ፣ ጎረቤት፣
ጓደኞች፣ ዘመድ-ወዳጅ ወገኖች ቀዳሚውን ኃላፊነት መሸከም ይጠበቅባቸዋል ብዬ አስባለሁ፡፡

የትግሉ ስልቶች…

‹‹የከፋ ጭቆና ቢኖርም ሥርዓቱን የተሸከሙት ብዙ ሰዎች ለረጅም ጊዜ ትብብር ከነፈጉት ጨቋኙ አገዛዝ ተዳክሞ በመጨረሻ መውደቁ
አይቀርም›› የሚለው ጄን ሻርፕ፤ የትብብር መንፈግ ፅንሰ-ሀሳብን የሰላማዊ ተቃውሞው ዋነኛው የትግል ማዕከል አድርጎ ያቀርበዋል፡፡
ለዚህ ስልት መተግበር ሀሳብን የማሰራጫ መንገዶች ያስፈልጋሉ፡፡ በይፋ የማይታወቁ የትግሉ መሪዎች/ቡድኖች፣ ሐሳቡ ጨቋኞቹን
ለመጣል በሚካሄደው መሬት አንቀጥቅ አብዮት ላይ እንዴት ከፍተኛ ሚና ሊኖረው እንደሚችል፣ ለማሕበረሰቡ ማስገንዘብ ይገባቸዋል፡፡
ይህን ማሕበረሰባዊ ጠንካራ መረዳት ለመፍጠርም፣ በራሪ ጽሑፎችን፣ ማሕበራዊ ድረ-ገፆችን፣ ሕብረ-ዜማዎችን፣ አጫጭር አነቃቂ
ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ 2

ፊልሞችንና የሞባይል ስልክ መልዕክት መለዋወጫ ዘዴዎችን ጨምሮ የተለያዩ የምስልና የድምፅ ሚዲያዎችን ማመቻቸት (መዘርጋት)
ይጠበቅባቸዋል፡፡ እነዚህ ከግብፅ እስከ ዩክሬን ተሞክረው የተሳኩ አማራጮችን በኢትዮጵያችንም ለመተግበር፣ በሚገባ መደራጀትና
በኃላፊነት መስራት በእጅጉ አስፈላጊና ግዴታ የመሆኑ ጉዳይ አያከራክርም፡፡ እንዲሁም ከሕዝበ-ሙስሊሙ የ‹‹ድምፃችን ይሰማ››
የተፈተነ እንቅስቃሴ ስኬታማ ተሞክሮዎችን ማጎልበትና ወደ ፖለቲካዊው ተቃውሞ መቀላቀል እንደሚቻል መዘንጋት የለበትም፡፡
የአደባባይ ተቃውሞ የሚፈቅደውን ሕገ-መንግስታዊ መብት በምልአት አንጠፍጥፎ መጠቀም ለሰላማዊ ትግሉ ዋነኛ መሰረት እንደሆነ
አምኖ መቀበልም ሌላው መረሳት የሌለበት ጭብጥ ነው፡፡ እነዚህን ኩነቶች ለመተግበር የማይነጣጠሉትን እንቅስቃሴዎችም በሶስት
በመክፈል በደምሳሳው እንመለከታቸዋለን፡፡

የአደባባይ እምቢተኛነት…

ዛሬ ላይ ስለመታገያ መንገዶቹ ብዙ ነጥቦችን ዘርዝሮ ማቅረቡ ላያስፈልግ እንደሚችል ይሰማኛል፡፡ ምክንያቱም በአገዛዝ ውስጥ
የሚመረጡ የትግል ስልቶች በይፋ ከመቅረብ ይልቅ፣ በተቃውሞው አደረጃጀት ጥልቅ ዝግጅት እንደየአውዱ እየተመረጡ ቢተገበሩ
የተሻለ ውጤታማ እንደሚሆኑ አምናለሁና፡፡ ሆኖም በዚህ መነሻነት ጥቂት ነጥቦችን ብቻ አንስቼ አልፋለሁ፡፡ በእነ ጄን ሻርፕ እና መሰል
የትግሉ መምህራን ተደጋግሞ የሚጠቀሰው ‹‹የአደባባይ መቀመጥ›› የሚባለው ለሰላማዊው አመፅ ግንባር ቀደም ተደርጎ ይጠቀሳል፡፡
ለረዘሙ ቀናት/ሳምንታት አደባባዮችን ሞልቶ፣ ተጨባጭ ፖለቲካዊ ማሻሻያም ሆነ መሰረታዊ የሥልጣን ሽግግር እስኪደረግ ድረስ
የመተካካት ስልት በተከተለ እና ግላዊ የዕለት ተዕለት የኑሮ መመሰቃቀሎችን ባገናዘበ (በእጅጉ ጉዳቶቹን በሚቀንስ) መልኩ በፈረቃ
ፕሮግራም የሚደረግ እንደሆነ ይታመናል፡፡ በትእምርትነትም የእስልምናን፣ የክርስትናን እና የአይሁድ እምነት ምልክቶችን ለመሰባሰቢነት
በመጠቀም፣ በዋና ዋና ግልፅ ሕዝባዊ የመሰባሰቢያ ስፍራዎች ላይ የሰላም ድንኳኖችን መዘርጋት፣ የመማፀኛ ፊርማ ማሰባሰብ፣ በሕንፃዎች
አናትና በግድግዳዎች ላይ ለውጥ የሚጠይቁ መፈክሮችንና ምስሎችን መለጠፍ፣ የመኪና ጥሩንባንና ሌሎች ከፍተኛ ድምፅ ሰጪ
መሳሪያዎችን ያለማቋረጥ ማስጮኽ፣ የቤት ውስጥ መቀመጥ፣ የሥራ፣ የትምህርትና የረሃብ አድማዎችን መምታት፣ በማሕበራዊ ጉዳዮች
ላይ ማደም፣ በየእምነት ተቋማቱ በጋራ ፀሎት ማድረግ… በዚሁ ስር የሚካተቱ ተግባራት ናቸው፡፡

በርግጥ ይህ ሁሉ ሲሆን የአገዛዙ መሪዎች ሕዝባዊ አብዮቱን በታጠቀው ኃይል ለመቀልበስ ሙከራ ማድረጋቸው የሚጠበቅ ነው፡፡
ይሁንና በዚህን ጊዜ ከፀጥታ አስከባሪዎች ጋር እሰጥ-ገባ ውስጥ ባለመግባት፣ ምንም አይነት አፀፌታዊ ግብረ-መልስ ባለመስጠት፣ በተንኳሽ
የቁጣ ቃላት በመጎነታተል ለማበሳጨት ባለመሞከር፣ ተቀጣጣይና ስለት ነገሮችን ከአካባቢው በማራቅ ወይም በፍፁም ባለመያዝ…
የተቀኙ ስልቶችን መከተል የሕዳሴ አብዮታችን መገለጫ ነውና፤ በዚሁ መንገድ መፅናት ግዴታ ይሆናል፡፡ በተጨማሪም ይህ አካሄድ
በአንዳንድ አገራት እንደተስተዋለው አጋጣሚውን በመጠቀም አብዮቱን ለመጥለፍም ሆነ ሰርገው በመግባት ወደ ደም-አፋሳሽ ነውጥ
ለመግፋት የሚሞክሩትን ለመከላከል ያስችላል፡፡

ሌላኛው ጭብጥ፣ የትግሉን ግብ በግልፅ ቋንቋ ካስቀመጡ በኋላ፣ የተለያዩ ሀገራትና ተቋማት ለሥርዓቱ የሚሰጡትን ድጋፍ
እንዲያቋርጡ መወትወት ነው፡፡ ቀጥታዊዎቹን ሰብአዊ ዕርዳታዎች ሳይጨምር ኢህአዴግ በቀዳሚነት የባጀት ድጋፎቹን ከነዚህ ሀገራትና
ተቋማት እንዳያገኝ ጠንካራ ዲፕሎማሲያዊ ጫና የሚካሄድበትን ስልት መቅረፅ በእጅጉ አስፈላጊ ነው፡፡ ከዚሁ ጋር ተያይዞ፣ አፈናውን
ለማራዘም በርትተው በሚሰሩት የሥርዓቱ ፊት-አውራሪዎች ላይ፤ የጉዞ ማዕቀቦችን ጨምሮ ሌሎች ወደ ድርድሩ ማዕቀፍ እንዲመጡ
የሚያስገድዱ ግላዊ ጫናዎች እንዲጠናከሩባቸው መጣር፣ ተጨማሪ የትግሉ መንገድ መሆን ይኖርበታል፡፡

አብዛኛዎቹ የአለማችን ጨካኝ አገዛዞችን ለታሪካዊ ሽንፈት የዳረገው ሌላው የመታገያ ስልት፣ አፋኝ ሕጎቻቸውን በግልጭ መጣስ መሆኑ
በቀዳሚነት የሚወሳ ነው፡፡ በእርግጥ ይህን መሰል የአደባባይ የኢ-ፍትሓዊ ሕጎች ጥሰት ብዙ ዜጐችን ለእስር ይዳርጋል፡፡ ሆኖም የሰላማዊ
አብዮት ውጤት መገለጫ፣ የዜጐች እስርን የመዳፈር ብርታት እንደሆነ ከመታወቁ አኳያ፣ ይህኛው አካሄድ ከፍተኛ ሚና አለው፡፡ በእኛም
ምድር እስርን የሚዳፈሩ ብርቱና ቆራጥ ጎበዛዝት በተበራከቱ ቁጥር፣ የተቃውሞ አድራጊዎች መጠን በሂደት እየጨመረ እንደሚመጣና
ግንባሩም ስጋት አድሮበት ከአፈና እርምጃዎቹ መቆጠቡ ስለማይቀር፣ ለምንፈልገው ሥርዓታዊ ሽግግር አስገዳጅ ፈቃደኝነት ውስጥ
ልንከተው እንደሚቻለን ማመን ተገቢ ይመስለኛል፡፡ ይሁንና ውጥረቱ እየበረታ በሄደ ቁጥር ሥርዓቱ ተቃውሞውን ለማክሸፍ በብዛት ወደ
እስር መላኩ አይቀሬ ቢሆንም ‹ስለኔ አታልቅሱ› እንዲል መጽሐፉ፣ በእርምጃው ሳይደናገጡ በአቋም በመፅናት ከአደባባዩ ሳያፈገፍጉ፣
ታሳሪዎቹን በጀግንነት እያወደሱ፣ ለእስር የሚዳርጉ ሕጎችን በመጣስ ጀግኖቹን መቀላቀልና ማጎሪያዎቹን አለቅጥ ማጨናነቅ አገዛዙን
ለማሽመድመድ ጠቃሚነቱ በተግባር የተሞከረ ስልት መሆኑን ማስታወስ ያሻል፡፡ ነፃነቱን በነፃ ያገኘ ከቶም ቢሆን የለምና! በሰላም ጊዜ
እንጂ በእንዲህ አይነቱ የንቅናቄ ወቅት እስር ቤት ቅንጣት ታህል የሚያስፍራ አለመሆኑን በልበ-ሕሊና ማሳደሩ ጠቃሚ ነው ብዬ
አስባለሁ፡፡

ኢኮኖሚያዊ ትብብር መንፈግ

ስለትብብር መንፈስ መንፈግ ጉዳይ አስቀድመን ልናነሳው የሚገባን ኢኮኖሚ ተኮር የሆነውን የትግል ስልት ነው፡፡ ይህ ሥርዓት
ለጭቆናው መሰረት ካደረጋቸው መካከል፣ በዝባዥ የምጣኔ-ሀብት ተቋማትን ማቋቋሙ አንዱ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ እናም የኢኮኖሚ
ትብብር መንፈግን ቀዳሚው የትግል አማራጫችን ብናደርገው የሕዳሴውን አብዮት ግቦች በአጭር ጊዜ ለማሳካት የማስቻሉ ዕድል የሰፋ
ይሆናል፡፡ ለዚህም በዋናነት ልናተኩርባቸው የሚገቡ ሁለት ጉዳዮች አሉ፡፡ አንደኛው በማዕከላዊ መንግስቱ በቀጥታ እንደሚመሩና
እንደሚደገፉ ከሚነገርላቸው ድርጅቶች፣ ምርቶችን ባለመግዛትና የምርት ሂደቱንም ከውስጥ በማጨናገፍ፣ እንዲዳከሙ ማድረግን
የሚመለከት ነው፡፡ ረዥሙ ትግል ከባድ ዋጋ እንደሚጠይቀን ከተማመንን፣ ለህልውናችን የቀን ተቀን ኑሮ እጅግ ወሳኝ የሆኑትን የምርት 3

ውጤቶች ከመንግስታዊ ተቋማቱ አለመግዛት፣ ሥርዓቱን ለማሽመድመድ ውጤታማ መሆኑ አይቀርም፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ፣ በእነዚህ
ተቋማት ውስጥ የሚሰሩ ሠራተኞችንና መሀከለኛ የአመራሩን አባላት፣ የምርት ሂደቱን እንዲያስተጓጉሉ በማግባባት፣ ተቋማቱን
በዝግመታዊ ሂደት አቅማቸውን ማድቀቅ አንዱ የትብብር መንፈግ አማራጭ ነው፡፡ ይህ መንገድ ከዛሬው ነባራዊ ሁኔታችን አንፃር
የማይቻል ቢመስልም፤ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ ‹‹በርግጥ! እንችላለን!!›› እንዲል፤ እኛም የነቃንለትን ሃሳብ ለመፈፀም የማንፈነቅለው
ድንጋይ እንደማይኖር በተግባር ማሳየት ይጠበቅብናል፡፡ ደግሞም በቀላሉ በማይደበዝዝ መነቃቃት ካልታደስን መጪው ጊዜ አደገኛ ይሆን
ዘንድ እንደመፍቀድ ይቆጥራልና፤ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች በሚገኙ መንግስታዊ የንግድ ተቋማት ውስጥ ያሉትን ሠራተኞች በአንድ
የግንኙነት መስመር በማስተሳሰር ሁኔታዎች ግድ ባሉ ቀን በተመሳሳይ ጊዜ በማንቀሳቀስ፣ ሥርዓቱን ክፉኛ ማዳካሙ ተግዳሮት የበዛ
አለመሆኑ አከራካሪ አይመስለኝም፡፡ የኢኮኖሚ ትብብር መንፈግን የግድ የሚያደርገው ሌላው ጉዳይ፣ ግብር (ታክስ) ያለመክፈል ሕዝባዊ
እምቢተኝነትንም ስለሚያጠቃልል ነው፡፡ የጭቆናው አገዛዝ ተጠናክሮ የቆመው በታክስ ሥርዓቱ ላይ መሆኑንም ሆነ ለሥልጣን ዕድሜ
ማራዘሚያው መጥቀሙን በቅጡ መገንዘብ ከቻልን ታክስ ባለመክፈል፣ የቆመበትን መሰረት መቦርቦር የሚቻልበት ዕድል መኖሩን
ማስታወስ አስፈላጊ ነው ብዬ አስባለሁ፡፡

ሁለተኛው ደግሞ የኢትዮጵያችን ነባራዊ ሀቅ፣ አብዮቶቹ ከተተገበረባቸው ሀገራት አንድ ለየት የሚል ገፅ ያለው ከመሆኑ ጋር የሚነሳ
ነው፡፡ ይኸውም የገዢው ግንባር አባላት ተከፋፍለው በሀገሪቷ ኢኮኖሚ የአንበሳውን ድርሻ መያዛቸው ነው፡፡ ከማዕድን ቁፋሮ እስከ
ጨርቃጨርቅ ኢንዱስትሪ፤ ከፋይናንሺያል ተቋማት እስከ አልኮል ምርቶች ድረስ የተቆጣጠሩበትን መንገድ ማዳከም፤ ሕዝባዊ ጉዳት
ሳይከተል ቀጥታ የሥርዓቱን የመጨቆኛ ምንጭ ማድረቁን ቀላል ያደርገዋል፡፡ በርግጥ አገዛዙ ከእነዚህ የፓርቲዎቹ ተቋማት ምንም አይነት
አገልግሎት ላለመጠቀም የሚደረገውን አድማ በመመዝመዝ፣ ሂደቱን በአንድ ቋንቋ ተናጋሪ ላይ ያነጣጠረና ብሔሩን ሆን ተብሎ ለመጉዳት
ታስቦ እንደተደረገ አስመስሎ የሚነዛውን መርዛም ፕሮፓጋንዳ ከወዲሁ ለማጨናገፍ፣ ከድርጅቶቹ ምርቶቹን ያለመግዛት ውሳኔ፣
ከማንኛውም ብሔር ጋር እንደማይገናኝ ማመን እና መተማመንን መፍጠር ቀዳሚው ተግባር መሆኑ ይኖርበታል፡፡ በ‹‹ኤፈርት›› የበለፀገች
ትግራይ፣ በ‹‹ዲንሾ›› ያደገች ኦሮሚያ፣ አልያም በ‹‹ጥረት›› የተጠቀመ የአማራ ክልል አለመኖሩን፣ መጀመሪያውኑ ከልብ ተገንዝበን
ከተንቀሳቀስን፣ ፓርቲ ተኮር ድርጅቶቹን ማግለል አስቸጋሪ አይሆንብንም፡፡ የተቃውሞ እንቅስቃሴው ቀጣይ ቅቡል መሪዎችም ይህን
ጭብጥ ሕዝቡ ዘንድ በሚገባ ማስረፅ አንዱ ኃላፊነታቸው መሆኑን ሊዘነጉት አይገባም፡፡

የገዥው ፓርቲ አባላት…

ሶስተኛው ልንዘጋጅበት የሚገባው ጉዳይ፣ በመጀመሪያው የአብዮቱ እርከን ለዘብተኞቹን የግንባሩ አባላት በእንቅስቃሴው እንዲሳተፉ
ማመቻቸት ነው፡፡ በተለይም ከድህረ-97ቱ የምርጫ ፖለቲካ ድቀት እና ይህን ተከትሎ በመጣው የተቃውሞ ስብስብ መዳከም የተነሳ፣
‹ፓርቲውን በአዝጋሚው መንገድም ቢሆን እየገሩ መሄድ ይቻላል› በሚል የተቀላቀሉ እንዳሉ ይታወቃልና፤ እነዚህን ወንድሞችና እህቶች
በሂደቱ ውስጥ ለማሳተፍ፣ የአብዮቱን መሪ ህልም እንዲያምኑበት ማድረጉ የግድ ነው፡፡ እነርሱን እያካተትን በተጓዝን መጠን፣ ሌሎቹም
የፓርቲው አባላት ትግሉን በመቀላቀል፣ የራሳቸውን ጥያቄዎች አንግበው ሥርዓቱ ወደመነጋገር እንዲመጣ ያስችሉታል ብዬ አምናለሁ፡፡
የታቀደ አብዮት ስኬቶችን ስንመረምር እነዚህን መሰል ክስተቶችንም የለውጡ አካል ማድረጉን መረዳታችን አይቀርም፡፡ በነገራችን ላይ
በመታደሳችን ዘመን ለቀደሙ ወንጀሎችም ሆነ ሀገራዊ ውድመቶች ሂሳብ ማወራረድን ታሳቢ ማድረግ ፍፁም አብዮቱን መጎተት
ከመሆኑም በላይ፣ የታሪካችንን አስቀያሚ ገፅ በመድገም ቁልቁል መዝቀጥ እንደሆነ መተማመን ይኖርብናል፡፡ ግባችን ኢትዮጵያን እያደሱ
ወደፊት ማራመድ እስከሆነ ዘንዳ፣ የተሻለ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን የመፍጠሪያው መንገድ ላይ ብቻ ማተኮር ብቸኛው መፍትሄ ነው፡፡
ያለፈው ዘመን ሰማዕታትን እየዘከርን፣ ለአጥፊዎቹ ምህረት እያደረግን በይቅርባይነትና በመቻቻል ላይ የምታብበውን ኢትዮጵያን
መመስረት የሕዳሴው አብዮት ግብ ሊሆን ይገባል፡፡

የንቅናቄው ፊት መሪዎች

ይህን የለውጥ መንፈስ በፊት መሪነት ማስተባበር የሚችሉ ጠንካራ የሲቪክ ተቋማት በሀገሪቱ ያለመኖራቸው ጉዳይ፣ ለሂደቱ መፍጠን
የግድ ሌላ አማራጭ እንድንፈልግ ያስገድደናል፡፡ በርግጥ አንዳንድ ወገኖች ለእንዲህ አይነቱ ጊዜ በሰላማዊ መንገድ የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ
ፓርቲዎችን መጠቀምን ይመክራሉ፡፡ ይህ ግን አደገኛና ያልተጠበቀ ክስረት ሊያስከትል የሚችል ይመስለኛል፡፡ ምክንያቱም ድርጅቶቹ
የየራሳቸው የተለያየ ዓላማ አንግበው የሚታገሉ በመሆኑ ከተሳታፊነት አልፈው በመሪነት መምጣታቸው፣ ሁነቱን ከሁሉን አሳታፊነት ወደ
ቡድንነት፤ ከዲሞክራሲያዊ ሽግግር ወደ ሥልጣን ነጠቃነት (መፈንቅለ መንግስት) የመቀየር አደገኛ ክስተት ውስጥ ሊያስገባው ይችላል፡፡
ይህ አካሄድ በሌሎች ሀገራት ለከሸፉ አብዮቶች በማሳያነት መጠቀሱንም ታሳቢ በማድረግ፣ ለእኛ ችግር መፍትሔውን አዲስ (ከዚህ ቀደም
ያልተሞከረ) አማራጭን ከራሳችን ወቅታዊ ሁኔታ አንፃር መፈለግ ላይ ማተኮሩ ይበጃል፡፡ በግሌም ይህንን ታላቅ ሀገራዊ ግዴታ ለመሸከም
የተሻሉ ናቸው ብዬ የማስበው ዩንቨርስቲዎቻችንን ነው፡፡ በመላ ሀገሪቱ በተመሳሳይ ወቅት መጀመር የሚኖርበትን የሕዳሴ አብዮት፣
ሁሉም መንግስታዊ ዩኒቨርስቲዎች የሚገኙበትን ከተሞች ጨምሮ አጎራባች አካባቢዎችን ለማስተባበር ኃላፊነት የሚወስዱበት መንገድን
ማማቻቸቱ የሚሳካበትን ስልት ከወዲሁ መቀየስ የሚቻል ይመስለኛል፡፡ ርግጥ ነው በዛሬው እውነታ ላይ ሆነን በተለይም የከፍተኛ
ትምህርት ተቋማት የገዢው ፓርቲ የፖለቲካ መናኸሪያ የመሆናቸውን ነገር ግምት ውስጥ አስገብተን ስናምሰለስለው፣ ሁነቶቹ አልጋ
በአልጋ ሊሆኑ እንደማይችሉ ከማንም የተሰወረ አይሆንም፡፡ ግና፣ በየተቋማቱ የየትኛውም ፓርቲ አባል ያልሆኑ ለውጥ አራማጅ
መምህራንና ተማሪዎች በራስ ተነሳሽነት በመሰባሰብ የማስተባበሩን ኃላፊነት ተረክበው ከፊት መስመር እንዲሰለፉ የማንቃትና ማብቃት
ሥራ ቢሰራ፣ አንድም እዚህ ግባ የሚባል ተግዳሮት ባለመኖሩ ሂደቱን ለማፋጠን ይጠቅማል፤ ሁለትም ከንቅናቄው ስፋት አኳያ ለከበደ
መስዋዕትነት የመዳረጉ አጋጣሚ እጅግ የጠበበ በመሆኑ ግንባር ቀደም ተሰላፊ ደፋሮችን ማግኘት አዳጋች አያደርገውም፡፡ ይህ ዕቅድ
የሚሳካ ከሆነ ደግሞ ዩኒቨርስቲዎቹ በዕኩል ውክልና የጋራ ማዕከል (አዲስ አበባ ለዚህ አመቺ ሊሆን ይችላል) አቋቁመው አብዮቱን
በሀገርና ሕዝብ ጥቅም አስተሳስረው መምራት እንደሚኖርባቸው እንደማይዘነጉት ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ 4

የአብዮቱ የመጀመሪያ ጥያቄዎች

ሕዝባዊ ንቅናቄው በሚገባ ተጠናክሮ ከቀጠለ በኋላ መንግስት እጁን ተጠምዝዞ እንዲተገብራቸው መነሳት ያለባቸው ቀዳሚ ጥያቄዎች
(ለለውጡ መደላድል የሚሆኑት) የሚከተሉት ቢሆኑ መልካም ነው፡- በመላ ሀገሪቱ ባሉ ማረሚያ ቤቶች የሚገኙ የፖለቲካ፣ የሕሊና እና
የሀይማኖት እስረኞችን ያለምንም ቅድመ ሁኔታ መፍታት፤ በውጪ ሀገር ያሉ ተቃዋሚ ድርጅቶች፣ ምሁራን፣ ጋዜጠኞች እና የመብት
ተሟጋቾች ያለልዩነት ወደ ሀገር ቤት ገብተው በነፃ እንዲንቀሳቀሱ መፍቀድ፤ ባለፉት ጥቂት ዓመታት የወጡ አፋኝ ሕጎችን መሰረዝ፤
በሀገሪቱ የመንግስት ምሥረታ ላይ የአፈና መዋቅር ሆኖ የሚያገለግለውን ምርጫ ቦርድ አፍርሶ አብዛሃ ኢትዮጵያዊን ሊያሳምን በሚችል ገፅ
እንደገና ማዋቀር፤ ለዴሞክራሲ ጠቃሚ የሆኑ የተለያዩ ተቋማትን ነፃ ማድረግ፤ የብዙሃን (የመንግስት) ሚዲያን እውነተኛ የሕዝብ ልሳን
የሚሆኑበትን አሰራር መዘርጋት፤ መከላከያ ሰራዊቱ፣ የደህንነት ሰራተኛው እና የፖሊስ አባላት በነቢብ ሳይሆን በገቢር ተጠሪነታቸውን
ለሕገ-መንግስቱ ማድረግ… ሲሆን፤ እነዚህ ሁኔታዎች ከተሟሉ በኋላ በ2007 ዓ.ም. የሚካሄደውን ምርጫ ለተጨማሪ አንድ አመት
በማራዘም፤ ለሁሉም ተወዳዳሪዎች (ለነባሮቹም ሆነ አዲስ ለሚደራጁት) መድረኩን ክፍት አድርጐ የሕዳሴውን አብዮት ለውጥ መተግበር
ይቻላል ብዬ አምናለሁ፡፡ እዚህ ጋ መዘንጋት የሌለበት ዋነኛው ጉዳይ አብዮቱ በራሱ በገዥው-ፓርቲ ውስጥ ያሉ በፖለቲካ ቀኖናዊነት
ያልተጠለፉና ሀገራዊ ለውጥ ፈላጊ የአመራር አባላት ‹የኢህአዴግ መንግስት ወይም ሞት!› የሚሉ ግትር ጓዶቻቸውን አግልለው፣ ይህንን
ኃላፊነት እንዲወስዱ ጫና ማድረግ ላይ የሚያተኩር እንጂ፤ በደፈናው ግንባሩን በጠላትነት ፈርጆ የሚያሳድድ አለመሆኑን ግንዛቤ
መውስድ ያስፈልጋል፡፡ የሕዳሴው አብዮታችን የ‹ጊሎትን› ማሽን የማይታጠቅና ልጆቹንም የማይበላ፤ በአጥፍቶ መጥፋት ጨዋታ ሕግ
የማይመራ መሆኑን ማስረገጥ ቀዳሚው ተግባር ይሆናል፡፡ ጎን ለጎንም የለውጡን (የጥያቄዎቹን) መፈፀም የሚከታተል ከንቅናቄው
አስተባባሪዎች፣ ከንግዱ ማሕበረሰብ፣ ከኃይማኖት ተቋማት፣ ከሲቪክ ማሕበራት፣ ከልሂቃኑ እና ከሀገር ሽማግሌዎች መካከል በተወጣጡ
ግለሰቦች የጋራ ምክር ቤት አዋቅሮ ቁጥጥር ማድረግ የሚቻልበትን አሰራር መቀየሱ ሌላኛው ጠቃሚ ክዋኔ ነው፡፡ ይህ መንገድ በድህረ-
ኢህአዴጓ ኢትዮጵያችን ፖለቲካዊና ማሕበራዊ ምስቅልቅሎሽ ቦታ እንዳይኖራቸው የመታደግ አቅምንም ለመገንባት ማስቻሉ መዘንጋት
የለበትም፡፡

የተባረከችዋ ቀን መቼ ትሆን?

ይህን መሰል የለውጥ ጥያቄ ማቅረቡ ሥርዓቱ ከሃያ ሶስት ዓመት በላይ ከመቆየቱ አኳያ የተቻኮለ እንደማይሆን አምናለሁና፤ ከላይ
ከተጠቀሱት ዋና ዋና አብዮታዊ ጉዳዮች አንፃር፤ እንዲሁም በአንድ ወቅት አቶ መለስ ዜናዊ ‹‹ልጄ ፋኖ ተሰማራ እንድትል አልፈልግም››
እንዳለው ሁሉ፤ ህወሓት የታሪካችን የመጨረሻው ‹‹ነፃ አውጪ›› ድርጅት ይሆን ዘንድ የሚታወጅበት ዕለትን ከወዲሁ መወሰኑ ላይ
ከተስማማን፣ የ2007ቱ ወርሃ መስከረም በሁለት ጉዳዮች ቢመረጥ የተሻለ ይመስለኛል፡፡ የመጀመሪያው በቀጣዩ ዓመት የሚደረገውን
አምስተኛ ዙር ሀገር አቀፍ ምርጫን የማራዘሙ አስፈላጊነት ከሕዝባዊ ጥያቄው መካከል ግንባር-ቀደም በመሆኑ ለአገዛዙ በቂ የጥሞና ጊዜ
መስጠት የማስቻሉ ጠቀሜታ ሲሆን፤ ሁለተኛው ደግሞ የአዲስ ዓመት ጅማሮ ከመሆኑ አኳያ ባሕላዊም ሆነ ስነ-ልቦናዊ መነቃቃት
የመፍጠር አቅሙ የራሱ በጎ አበርክቶ ይኖረዋል ተብሎ ስለሚታሰብ ነው፡፡

ከሞላ ጎደል ለሶስት ሳምንታት ያህል የተነጋገርንባቸው እነዚህ ታላላቅ አጀንዳዎች እውን ይሆኑ ዘንድ ቀጠሮውን በልቦናችን ይዘን፣
ራስን በውስጥ ዝግጅት ማሰናዳቱ ለነገ የማይተው የቤት ስራችን መሆኑንም ጨምሮ መረዳት ያሻል፤ በዚህም የሕዳሴያችን ንቅናቄ እንደ
ቀዳሚዎቹ ሁለት አብዮቶች አዲስ መዘዝ፣ ሳይሆን አዲስ ተስፋ እንዲያመጣ እናስችላለን ብዬ አስባለሁ፡፡ በመጨረሻም ያቺ ትንሳኤ
አብሳሪ ዕለት በኢትዮጵያችን ምድር ከቶም ቢሆን አቻ የላትምና፣ በአያሌ ናፍቆት ስለመጠበቋ ዛሬ ላይ እንዲህ መመስከሩ ከምኞት
የተሻገረ መሆኑን አስረግጬ ብናገር ማጋነን አይሆንም፡፡

ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር!

ኢትዮሚድያ – Ethiomedia.com
June 8, 2014

Advertisements

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s