Ethiopia: ተወዳጇ ፍትህ ጋዜጣ ዳግም ለንባብ ልትበቃ ነዉ

Imageታማኝ የዉስጥ ምንጮች ዛሬ ሰኞ 30/11/2004 እንደጠቆሙት ከህትመት ታግዳ ብዙ ስታወዛግብ የነበረችዉ ተወዳጇ ፍትህ ጋዜጣ በአሳታሚዎቿና በመንግስት አካላት መካከል በተደረገ ተከታታይ ድርድር አርብ በ4/12/2004 ወደ ገበያ ልትመለስና ለንባብ ልትበቃ ነዉ፡፡

እንደሚታወቀዉ ጋዜጣዋ የጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊን መታመምና ከዓይን መሰወር ምክንያት በማድረግ ይዛዉ ልትወጣዉ ከነበረዉ ፅሁፍ ጋር በተያያዘ እንዳትሰራጭ ተከልክላ የነበረ ሲሆን ፤ ህትመቱም እንዲቃጠል ተወስኖ ነበር፡፡  ቆይቶም አሳታሚዎቿ ባልተገኙበት ችሎት ፍፁም ግራ በሚያጋባ ሁኔታ ጭራሹን ከህትመት ታግዳ ነበር፡፡

የጋዜጣዋ ከህትመት መታገድ በብዙ ደንበኞቿ ዘንድ ትልቅ ቅሬታን ፈጥሮ የነበረ ሲሆን ፤ ብዙ አካላትም እገዳዉን በሞት አፋፍ ላይ ባለዉ በነፃዉ ፕረስ ላይ የተፈፀመ ጭፍን እርምጃ ብለዉ ኮንነዉት ነበር፡፡

በተለይም ከጋዜጣዋ መታገድ ጋር በተያያዘ በፍትህ ሚኒስትርና በብርሀንና ሰላም መካከል የነበረዉ ግራ የሚያጋባ የሀሳብ ተቃርኖ ብዙዎችን ያሳዘነና ያሳፈረ ነበር፡፡

ፍትህ ጋዜጣ በኢትዮጵያ ዉስጥ ከሚሰራጩ በጣት ከሚቆጠሩ የነፃ ፕረስ ዉጤቶች ዉስጥ አንዷ ስትሆን ፤ የህዝብን የልብ ትርታ ባዳመጡና የመንግስትን ተግዳሮቶች በነፃነት በሚነቅሱ ፅሑፎቿ በብዙኃኑ ዘንድ እዉቅናንና ተወዳጅነትን ማትረፍ  የቻለች ብቸኛ ጋዜጣ ናት፡፡

Leave a comment